በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ በማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ከ5 ነጥብ 6 ቢሊየን በላይ ብር መሰብሰቡን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሀብት አሰባሰብ አስተዳዳር እና አጋርነት ዳይሬክቶሬት የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፃም ግምገማ እና የ2108 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።

በመክፈቻ ፕሮግራሙ የተገኙት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መልካሙ ጌትነት እንደገለፁት፤ ማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ግቡን እንዲያሳካ ዋነኛው እና መሰረታዊው ጉዳይ ማኅበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ ሀብት መሰብሰብ ነው።
በዚህም በበጀት ዓመቱ ለማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን አገልግሎት የሚሆን ከ5 ነጥብ 6 ቢሊየን በላይ ብር መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።

የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድንን ጥቅም እና አገልግሎት ማኅብረሰቡ በሚገባ በመረዳቱ ምክንያት ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ባሳተፈ መልኩ ሀብት የመሰብሰብ ተግባሩ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
መክፈል ለማይችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ መንግስት በመሸፈን የተሰበሰበውን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ቀጣይነቱንም በተገቢው ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው ሲሉ ገልፀዋል።
በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የሀብት አሰባሰብ አስተዳደር እና አጋርነት ዳይሬክቶሬት በበጀት ዓመቱ ለ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን አባውራ እና አማውራዎች አገልግሎቱን መስጠት እንደተቻለ የገለፁት ደግሞ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ በምክትል ቢሮ ኃላፊ ደረጃ የቢሮው ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ክሽን ወልዴ ናቸው።

የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን በክልሉ በ2003 ዓ.ም በሶስት ወረዳዎች መጀመሩን አንስተው፤ አሁን ግን በአማራ ክልል በሁሉም ወረዳዎች አገልግሎቱን እየሰጡ እንደሆነ ገልፀዋል ሲል የዘገበው ኢፕድ ነው፡፡












