የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) የባሕር በር ተጠቃሚነትን በሚመለከት የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ጉዞ ከግማሽ መንገድ በላይ መራመዱን ገለጹ።
ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች ስኬት በማስመዝገብ ላይ ትገኛለች ብለዋል። በከተማ እና የገጠር ኮሪደር ልማት አዲስ ምዕራፍ ተክፍቷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት ዓለም አቀፋዊ ተፅእኖ መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ መገንባቱን ገልጸዋል።
በማኅበራዊ ዘርፍም የሰለጠነ የሰው ኃይል እና በበጎነት መርሕ የሚመራ መልካም ዜጋ በማፍራት ረገድ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል ። በሜጋ ፕሮጀክቶች ረገድ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከፍጻሜው ጫፍ መድረሱንም ነው ያነሱት።
ኢትዮጵያ በሁሉም እንቅስቃሴዎች እያገኘች ያለውን ጉልህ ስፍራ ለማስተጓጐል፤ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ከሚዘውሯቸው የውስጥ ባንዳዎች ጋር በመተባበር ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ፈተና ተከፍቷል ብለዋል።
የኢትዮጵያን ገፅታ ለማጠልሸት የሚደረገውን እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን በዲጂታል ምህዳር በመተባበር የመመከት ሥራ እንደሚጠበቅባቸውም ሚኒስትሩ አመላክተዋል። ግጭት እና ብጥብጥን የኢትዮጵያ ማዳከሚያ ስልት አድርገው የሚጠቀሙ ኃይሎችን አላማ በመረዳት፤ ዜጎች የሀገርን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ በጋራ እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል።
ሚኒስትሩ መልእክታቸውን ያስተላለፉት በዲጂታል ኢቢሲ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ነው።












