አውስትራሊያ ለፍልስጤምን መንግስት እውቅና ለመስጠት ማቀዷን አስታወቀች::
የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዝ፤ አውስትራሊያ በመጪው መስከረም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለፍልስጤም መንግስት እውቅና እንደምትሰጥ አስታውቀዋል። አውስትራሊያ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ካናዳ በመቀጠል ለፍልስጤም መንግስት እቀውቅና ለመስጠት ካቀዱ ሀገራት አንዷ ሆናለች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አልባኒዝ እንዳሉት መንግስታቸው ለፍልስጠየም እውቅና ለመስጠት ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጡን ገልጸው፤ ትጥቅ መፍታት፣ አጠቃላይ ምርጫ ማካሄድ፣ የእስራኤልን ህልውና የመኖር መብት መቀበል የሚሉት የቀረቡ ቅድመ ሁኔታዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች እንደሚተገበሩ ከፍልስጤም አስተዳደር (PA) ቃል እንደተገባላቸው ነው የተናገሩት፡፡ ከፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ “ሃማስ” በማንኛውም የወደፊት የፍልስጤም መንግስት ውስጥ ምንም አይነት ሚና እንደማይኖረው ማረጋገጫ ተሰጥቶናልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ይህ እርምጃ “የእድል ጊዜ” ሲሉም የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውስትራሊያ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመሆን ይህንን እድል ለመጠቀም እንደምትሰራ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። አልባኒዝ “በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን የአመፅ አዙሪት ለመስበር፤ በጋዛ ውስጥ ያለውን ግጭት፣ ስቃይ እና ረሃብ ማቆም እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ስፔን፣ አየርላንድ እና ኖርዌይ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የእርቅ ስምምነት ለማምጣት ይረዳል በሚል ተስፋ ለፍልስጤም እንደ ሀገር በይፋ እውቅና ሰጥተዋል። በአሁኑ ጊዜ ፍልስጤም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አባል ከሆኑት 193 ሀገራት መካከል በ147ቱ እውቅና ተሰጥቷታል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።
በ ሰላማዊት ወልደገሪማ












