የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው አል-ሺፋ ሆስፒታል ላይ ባደረሰው ጥቃት አምስት የአልጀዚራ ጋዜጠኞች መገደላቸው ተገለጸ ።
የቴሌቪዥን ማሰራጫ ጣቢያ አልጀዚራ ባወጣው መግለጫ መሰረት አናስ አል-ሻሪፍ እና መሐመድ ቀሪቂ የተባሉ ሁለት ሪፖርተሮች እና ኢብራሂም ዛሄር፣ መሐመድ ኑፋል እና ሞአመን አሊዋ የተባሉ የካሜራ ባለሙያዎች በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን ነው ይፋ ያደረገው።
ጥቃቱ በተፈጸምበት ወቅት እነኚህ ጋዜጠኞች በሆስፒታሉ ለጋዜጠኞች በተዘጋጀ ድንኳን ውስጥ እንደነበሩ አልጃዚራ ዘግቧል። አልጃዚራ በሰጠው መግለጫ “ዒላማ ያደረገ ግድያ ፣ የፕሬስ ነጻነት ላይ የተፈጸመ ሌላ ግልጽ እና ቀድሞ የታቀደ ጥቃት” ነው ሲል አስታውቋል።
ከጥቃቱ በኋላ የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት (IDF) በቴሌግራም ባሰራጨው መረጃ አናስ አል-ሻሪፍን የተባለው ሪፖርተር ማጥቃቱን አረጋግጦ፣ “በሐማስ ውስጥ የአሸባሪዎች ሕዋስ መሪ ሆኖ አገልግሏል” ሲል ገልጿል ።
የአል ጃዚራ ማኔጂንግ ኤዲተር የሆኑት መሐመድ ሙዓወድ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “ጋዜጠኞቹ የተገደሉት በድንኳናቸው ውስጥ ነው፤ ከጦር ግንባር እየዘገቡ አልነበረም” ብለዋል። “የእስራኤል መንግስት ከጋዛ ውስጥ የሚዘግቡ ማናቸውንም የዜና ማሰራጫዎች ድምጽ ማጥፋት ይፈልጋል” ሲሉም ተናግረዋል።
ከተገደሉት ጋዜጠኞች አንዱ የሆነው አናስ አል-ሻሪፍ “በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ምን እየተፈጠረ እንዳለ ዓለም እንዲያውቅ ድምፅ” የነበረ እውቅና ያለው ጋዜጠኛ ነበር ሲል የእስራኤል መግለጫ ውድቅ አድርጓል።
በጦርነቱ ወቅት እስራኤል ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች በነፃነት ወደ ጋዛ ገብተው እንዳይዘግቡ መከልከሏ ይታወሳል ።
ዘገባው የቢቢሲ እና አልጀዚራ ነው
በ ሰላማዊት ወልደገሪማ












