የፕላስቲክ ምርቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ካልተደረገ በአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንደሚበረታ እየተገለጸ ነው፡፡ ሀገራት ፕላስቲክ የሚያሳድረውን ቀውስ በማጤን በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው ይገለጻል፡፡
እንደ ተመራማሪዎች ገለጻ የፕላስቲክ ምርት ከጊዜ ወደ ጊዜ ተፅዕኖው እየበረታ ሲሆን በዓለም ላይ በሚገኙ ውቅያኖሶች ወደ 200 ትሪሊዮን የሚጠጉ የፕላስቲክ ቁርጥራጮች ይገኛሉ፡፡ ዓለም አቀፍ ስምምነት ካልተቀየረ በ2060 የፕላስቲክ ቆሻሻዎች በሦስት እጥፍ እንደሚጨምሩ የተባበሩት መንግስታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም ይገልጻል፡፡
ለዚህም ነው 184 ሀገራት ተወካዮችን በጄኔቫ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፅህፈት ቤት በጉዳዩ ላይ እየመከሩ የሚገኙት፡፡ መድረኩ ሊጠናቅ 4ቀናት የቀሩት ሲሆን የፕላስቲክ ብክለትን ለመቀነስ የሚረዱ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ይቀመጥበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የውይይት መድረኩን በይፋ ያስጀመሩት የኢኳዶር ዲፕሎማት ሉዊስ ቫያስ ቫልዲቪሶ በፕላስቲክ ላይ የሚሰራው የመንግስታቱ ተደራዳሪ ኮሚቴ ዓለም አቀፍ ቀውስን ለመፍታት ኃላፊነት እንዲወስድ አሳስበዋል። በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተሰባሰቡት ሀገራት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠጥ አሰራራቸውን ሊያጤኑ እንደሚገባቸው ተገልጿል፡፡
በመድረኩም ከፕላስቲክ ዲዛይን እስከ ቆሻሻ አወጋገድ፣ አመራረት፣ ፕላስቲክ መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል እና በታዳጊ ሀገራት የቆሻሻ አሰባሰብን በገንዘብ መደገፍ በሚሉ ቴክኒካል ጉዳዮች ውይይት መደረጉን ተመላክቷል፡፡
እንዲሁም የአካባቢ እና የጤና ጠንቅ በሆኑ ፕላስቲክ ማምረቻ ኬሚካሎች ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን ከጤና ጋር በተገናኘም የዓለም ማህበረሰብ ከ1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ለሚደርስ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ መዳረጉ ተጠቁሟል፡፡
የፕላስቲክ ብክለት በየብስና በውሃ አካላት ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑ ተገልጾ በፈረንጆቹ 2060 የአለም አቀፍ የፕላስቲክ ምርት በሦስት እጥፍ ሊጨምር ይችላልም ተብሏል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2022 ሀገራት ቆሻሻውን እና አንዳንድ ፕላስቲኮች የያዙትን ጎጂ ኬሚካሎች ለማስወገድ በህግ አስገዳጅ ስምምነት ለማዘጋጀት ቢስማሙ ተግራዊነቱ ግን እምብዛም መሆኑ ይገለጻል፡፡
ከፈረንጆቹ ነሀሴ 5 እስከ14 ለ10 ቀናት በጄኔቫ እየመከረ የሚገኘው መድረኩ የሀገራት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች እና የኢንዱስትሪ ተወካዮች እየተሳተፉበት ነው፡፡
በ-ሰላም ይልማ












