በተባበሩት መንግስታት አዘጋጅነት ቱርክሜኒስታን አዋዛ ከተማ ውስጥ በተካሄደው የባህር በር የሌላቸው ታዳጊ ሀገራት (LLDC) ጉባኤ ላይ የተገኘው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከቱርክሜኒስታን የፓርላማ ዋና አፈ-ጉባኤ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቷል።
በውይይቱም የተከበሩ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር) የውጭ ግንኙነትና ሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ፣ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በጂኦግራፊያዊ አቀማመጣቸው ምክንያት ለተለያዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መጋለጣቸው አግባብነት የሌለው መሆኑን አንስተው ይህ ጉባኤ ተጨባጭ መፍትሄ ያመጣል ብለው እንደሚጠብቁ ገልፀዋል፡፡
አያይዘውም ጉባኤው ይህንን ለመቀየር “የአዋዛ የድርጊት መርሃ ግብር” (Awaza Programme of Action) ማዘጋጀቱን ጠቁመው የድርጊት መርሃ ግብሩን ሀገራት በአግባቡ ከተገበሩት ከባህር በር ጋር በተያያዘ ችግሮችን ለመፍታትና ተጨባጭ ውጤት ማምጣት ይችላል ብለዋል።
በተጨማሪም የተከበሩ ፈትሂ (ዶ/ር) ኢትዮጵያና ቱርክሜኒስታን የፓርላማ ወዳጅነት ቡድኖችን ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር በጋራ ለመስራት ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውንና ልምድ ልውውጥ በማድረግ በተለይም አለም አቀፍ ይዘት ያላቸውን ችግሮችን በትብብር መፍታት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሚንስትር ክቡር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የመሰረተ ልማት ዝርጋታና ዘመናዊ የንግድ ኮሪደሮችን መፍጠር እና ማስፋፋት ላይ ኢንቨስት ማድረግና በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
አክለውም እነዚህ ኮሪደሮች ለዘላቂ ልማት ግቦች የሚውሉ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ያልሆኑ እና ለምግብ ዋስትና፣ ለታዳሽ ኃይልና ለአካባቢ ጥበቃ የሚረዱ መሆን እንዳለባቸው አንስተዋል።
አያይዘውም ከጎረቤትና ትራንዚት ሀገራት፣ የልማት አጋሮችና አለም አቀፍ ተቋማት ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር የንግድ እንቅስቃሴን ለማስፋፋት ወሳኝ መሆኑ ገልፀዋል – ዶክተር አለሙ።
የቱርክሜኒስታን ፓርላማ አፈ-ጉባኤ ዲ. ጉልማኖቫ በበኩላቸው ጉባኤው በሀገራቸው መካሄዱን ከታላቅ ክብርና እምነት አንፃር እንደሚመለከቱት ገልጸው የኢትዮጵያ ልዑክ በጉባኤ ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረጉ አመስግነዋል።
አፈ-ጉባኤዋ ፓርላማዎች የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የልማት ዕቅዶችን ወደ ህግ ማዕቀፍና ተግባራዊ እርምጃ በመቀየር ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ገልፀው በሁለቱ ሀገራት ፓርላማዎች መካከል ያለዉን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችሉ እቅዶችን በመንደፍ እንደሚሰሩም ገልፀዋል።
ለአምስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው አለም አቀፉ ታዳጊ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት ጉባኤ በዛሬው ዕለት መጠናቀቁን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።












