አሻራቸው ዘመን ተሻጋሪ ከሆኑ ጉልህ እና ዓለም አቀፋዊ የታሪክ ክስተት ከተከነወነባቸው ቀናቶች አንዱ የዛሬው ዕለት ነው ።
ዛሬ ጋሊልዮ ጋሊሊ ቴሌስኮፕ በመገንባት፣ ለቬኒስ ሴኔት የቀረበበት ታሪካዊ ዕለት ነው። ስለዚህ ክስተት ጥቂት እንንገራችሁ! ጋሊልዮ ጋሊሊ እ.አ.አ በ1564 በጣሊያን ፒዛ ከተማ የተወለደ የሥነ ፈለክ ተመራማሪ፣ የፊዚክስ ሊቅ እና መሐንዲስ ነው።
በሳይንሳዊ አብዮት ውስጥ ቁልፍ ሰው በመሆኑ የዘመናዊው ሳይንስ አባት ተብሎ ይታወቃል ። በመጀመሪያ በፒዛ፣ በኋላ ፓዱዋ ዩኒቨርስቲዎች የሂሳብ ፕሮፌሰር ነበረ። የጋሊልዮ ዘመን ተሻገሪ ስራው በቴሌስኮፕ ከሚሰራው ስራ ጋር በእጅጉ የተያያዘ ነበር።
ቴሌስኮፕ መሣሪያውን የፈለሰፈው እሱ ባይሆንም በመሣሪያው ላይ ጉልህ የሆነ ማሻሻያ በማድረግ እና በሳይንሳዊ መንገድ ገጸ ሕዋን ለመመልከት የተጠቀመው እርሱ ነበር። ከምልከታዎቹ መካከልም የጨረቃ ገጽታዎች እና ሌሎች ፕላኔቶች በፀሐይ ዙሪያ እንደሚዞሩ የሚያትቱ የፀሐይ ስርዓት ሄሊዮሴንትሪክ ሞዴል ጠንካራ ማስረጃዎችን ማቅረብ ችሏል፡፡
ይህም በወቅቱ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሚደገፈውን የጂኦሴንትሪክ ሞዴል አስተምህሮ በመገዳዳሩ፣ ክስ ቀርቦበት በቀሪው የሕይወት ዘመኑ እስራት ተፈረደበት። እ.ኤ.አ. ኦገስት 8 በዛሬዋ ቀን 1609 ጋሊልዮ ስልታዊ እና ሥራውን የሚገልጽ እንቅስቃሴ በማድረግ የራሱን ቴሌስኮፕ ገንብቶ፣ ለቬኒስ ሴኔት ለማቅረብ ወደ ቬኒስ ተጓዘ።
ክስተቱ የተካሄደው ካምፓኒል ዲ ሳን ማርኮ በሚባለው የከተማው ታዋቂ የደወል ማማ ላይ ነው። መሳሪያው መርከቦች በአይን ከመታየታቸው በፊት በርቀት ከሰዓታት ቀደም ብሎ እንዴት እንደሚለይ በማሳየት ጋሊልዮ የቴሌስኮፑን ወታደራዊ እና የንግድ ጠቀሜታውን ለሴናተሮች አስረዳ ።
ይህም ጋሊሊዮ የዘመናዊ የሳይንስ አባት ከመሆንም አልፎ ስለ ገጸ ሕዋው ያለውን ግንዛቤ እንደገና መልክ ያስያዘ ዓለም አቀፋዊ የታሪክ ክስተት ነው።












