የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የክረምት ወቅት አጋማሽ የአየር ጠባይ ተጽእኖ በመገምገም፤ በቀሪው ክረምት ወቅት የሚጠበቀው የአየር ጠባይ ሁኔታ አስመልክቶ ማብራራያ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ ኢንስቲትዩቱ የክረምት ወቅት የሚኖረውን የዝናብ ሁኔታ ባስቀመጠው ትንበያው መሰረት የአየር ጸባይ መስተዋሉን ገልጸዋል። በሰኔና ሀምሌ ወራት 227 ጣቢያዎች ከፍተኛ የዝናብ መጠን ማስተናገዳቸውን በማንሳት ይህም ከባለፉት ዓመታት ሲነጻጻር ከፍተኛ እንደነበር ጠቁመዋል።
ዓለም አቀፍ የሚቲዎሮሎጂ ክስተትና ያማከለና የኢትዮጵያን የአየር ሁኔታን መሰረት ተደርጎ የተቀመጠው ትንበያ በቀሪ የክረምት ወራት ከባድ ዝናብ ሊከሰት እንደሚችል ነው የተገለጸው።
በነሃሴ ወር በሰሜን ምስራቅ፣ በሰሜን፣ በመካከለኛዉ፣ በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ የሃገሪቱ ቦታዎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የተገለጸ ሲሆን ሁኔታውን ያገናዘበ ስራ የሚጠይቅ መሆኑ ተነስቷል።
በዚህም የአፈር መሸርሸር እና የመሬት መንሸራተት ፣ንፋስ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ መሰል አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ተመላክቷል። የክረምት የዝናብ አገባብ ከደቡብ ምዕራብ ተነስቶ ሰሜን ምዕራብና ምስራቅ እየተስፋፋ መምጣቱ ነው የተጠቆመው።
የዝናብ መጠኑ ከፍተኛ መሆን የአከባቢ ጥበቃ ስራን ለማከናወን ና መሰል ስራዎችን ለማከናወን ረድቷል ተብሏል።
በ-ሰላም ይልማ












