ርዋንዳ ከአሜሪካ ስደተኞን ለመቀበል ተስማማች።
ይህም ሶስተኛዋ አፍሪካዊት አገር ያደርጋታል። ርዋንዳ 250 የሚሆኑ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከአሜሪካ እንደምትረከብ አረጋግጣለች። የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መጠነ ሰፊ ስደተኞን ወደ ተለያዪ አገራት የመመለስ ዘመቻ እና ውጥን አንዱ ክፍልም ነው።
የርዋንዳ መንግስት ቃል አቀባይ ዮላንዴ ማኮሎ አገራቸው በመቶዎቹ የሚቆጠሩ ስደተኞችን እንደምትቀበል ይፋ አድርገዋል። ከደቡብ ሱዳን እና ኢስዋቲኒ ቀጥሎ ርዋንዳ ዜጎችን ከአሜሪካ በመቀበል ሶስተኛዋ አፍሪካዊት አገር ሆና ተመዝግባለች።
የትራምፕ አስተዳደር ስደተኞችን ወደ ሶስተኛ አገር አሳልፎ መስጠቱ በሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ከፍተኛ ትችት እየተሰነዘረበት ነው። ርዋንዳ በሰብዓዊ መብት ጥሰት አሉታዊ ስም እንዳላት እየታወቀ፣ ወደ ኪጋሊ ፍልሰተኞችን መላክ አደገኛ ነው በሚልም ትራምፕ ይወቀሳሉ።
በሌላ በኩል የተለያየ ወንጀል የፈጸሙ እና አደገኛ ባህሪ ያላቸው ሰዎች መከማቻ አፍሪካን እያደረጓት ነው በሚልም የሚከሱ አሉ ሲል አልጀዚራ ዘግብዋል።
በ-ቢኒያም ካሴ












