ጉባኤው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያላቸውን ትብብር ከማጠናከር ባለፍ በቅርበት ለመነጋገር መድረክ የሚፈጥር ነው ተብሏል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጎንደር ዩንቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) የከፍተኛ ትምህርት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የለውጥ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል ብለዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወሳኝ ተልዕኮ አንዱ ጥናትና ምርምር መሆኑን ያነሱት ፕሬዚዳንቱ ይህንንም ለማጠናከር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የሚካሄደው ጉባኤ ወሳኝ ነው ብለዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሹኔ ይህ ጉባኤ የተዘጋጀው በሪፎርም ላይ በሚገኘው የትምህርት ስርዓት እንዲሁም የጎንደር ዩንቨርሲቲ 70 አመት እንዲሁም የማስተማሪያ ሪፈራል ሆስፒታል 100 ዓመት በሚከበርበት ወቅት በመሆኑ ለየት ያደርገዋል ብለዋል።
ትምህርት በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወዳዳሪ፣ የበለፀገች፣ ሉዓላዊት፣ ዴሞክራሲያዊ እና ፍትሃዊ የሆነች ኢትዮጵያን ለመገንባት ቁልፍ ነው ያሉ ሲሆን ለዚህም እንደዚ አይነት መሰል መድረኮች ወሳኝ መሆናቸውን ገልፀዋል። መድረኩ ዩንቨርሲቲዎች ልምድ የሚለዋወጡበት እደሚሆንም ተመላክቷል።
የጎንደር ዩንቨርሲቲ ከትምህርት ሚኒስትር ጋር በመሆን ባዘጋጀው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የለውጥ ምክር ቤት ዓመታዊ ጉባዔ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች እና ምክትል ፕሬዝዳንቶች፣ የመምህራን ማህበር አመራሮች ተገኝተዋል።
ሄርሜላ ፍቃደ(ከጎንደር)












