August 2, 2025
የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ባለፈው አንድ ዓመት ያከናወነውን ተግባርና የሠራተኞች ቀንን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው መርሃ ግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትተመስገን ጥሩነህ አስጀምረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የባቡር መሠረተ ልማት ከዘረጉ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗን ያስታወሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ቀዳሚ የመሆኗን ያህል በባቡር መሠረተ ልማት እርስ በርስ ሳትተሳሰር ቀርታለች ብለዋል፡፡ ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ የጀመርነውን አለማጠናቀቅ እና የቀጣይነት ችግር ዋናው ፈተናችን ሆኖ በመዝለቁ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር የታሰበውን ያህል አገልግሎት ሳይሰጥ፣ የሠራተኞችን ደመወዝ መክፈል ተስኖት የመንግሥት ዕዳ ሆኖ መቆየቱንም ጠቁመዋል፡፡ ይህንን ተከትሎም መንግስት ባለፉት ዓመታት የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡

በተለይም የባቡር መሥመሩን ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ ማስተዳደር ከጀመሩበት ባለፈው አንድ ዓመት ወዲህ አሠራሩ እንዲዘምንና እንዲቀላጠፍ ስለመደረጉ ገልፀዋል፡፡ የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትርንስፖርት ከፍተኛ መጠን ያለውን ጭነት እና ተሳፋሪን በአንድ ጊዜ በማጓጓዝ ላይ እንደሚገኝ በማንሳትም የሀገሪቱን የገቢና ወጪ የንግድ እንቅስቃሴ በማሣለጥ ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ስለመሆኑ አሳውቀዋል፡፡

የጀመርናቸውን የባቡር መሥመር ግንባታዎች የነበረባቸውን ችግር በጥናት በመፍታት የሚቀጥሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይጠበቅብናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚያም አልፈን ኢትዮጵያን የዘመናዊ ባቡሮች ሀገር ማድረግ አለብን ሲሉ ገልፀዋል፡፡ የባቡር መሥመሮች የአገራችንን ዕድገት ባገናዘበ ደረጃ ኢትዮጵያን በውስጥም በውጭም እስኪያገናኙ ድረስ፣ የጀመርነው የባቡር ዘርፍ ቀጣይነት እንዲኖረው በትጋት መስራት ይገባናልም ብለዋል፡፡













