የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ4 ኪሎ የገበያ ማዕከልን እና መኪና ማቆሚያን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል፡፡
በመድረኩ ባደረጉት ንግግር አዲስ አበባን ከቀድሞ ታሪኮቿ ጋር በማጣጣም ዘመናዊ ከተማ በማድረግ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡ የከተማዋ ታሪካዊ ስፍራ እና የድል ሀውልት መገኛ የሆነውን የ4 ኪሎ አደባባይ አካባቢን መልሰን ገንብተን የገበያ ማዕከልን፣ መኪና ማቆሚያን እና 4 ኪሎ ፕላዛን በመገንባት ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ነው ያሉት፡፡
ፕሮጀክቱ ከመሬት በታች የተገነቡ ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ከ100 በላይ ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ የሚያስተናግድ የመኪና ማቆሚያ እና ለተለያዩ ዝግጅቶች የሚውል በአንድ ጊዜ 5 ሺህ ሰዎችን መሰብሰብ የሚያስችል ፕላዛን ያካትታል፡፡ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩ እና የቱሪዝም ፍሰቱን ትልቅ አስታዋፅኦ እንዳለው ነው ከንቲባ አዳነች የገለጹት፡፡
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ በምዕራፍ አንድ እና ሁለት በከተማዋ የተሰራው የኮሪደር ልማት የመኪና ማቆሚያ እና ሌሎች ተያያዥ ፕሮጀክቶችን በማካተት መሰራቱን አውስተዋል፡፡ ፕሮጀክቶቹም ለማህረሰቡ የኢኮኖሚ ምንጭ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የተሰሩ የልማት ስራዎች የቀደመውን ታሪክ በጠበቀ መልኩ እሴት ተጨምሮባቸው መሰራታቸው ነው የተገለጸው፡፡
በ-ሰላም ይልማ












