የቀድሞው የእንግሊዝ ታሪካዊ ተጫዋች እና የቴሌቪዢን ዝግጅት አቅራቢ ከቢቢሲ የተሰናበተበትን እውነተኛ ምክንያት ከሁለት ወር በኋላ ተናግሯል።
ጋሪ ሊንከር ፍላግሺፕ ፉትቦል የተባለ ተወዳጅ ፕሮግራም የነበረው ሲሆን፣ባሳለፍነው የግንቦት ወር ከሚዲያው መውጣቱን መግለጹ ይታወሳል።
ሊንከር ከቆይታ በኋላ እንደገለጸው በወቅቱ እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ጥቃት የሚያወግዝ ምስል ለተከታዮቹ በማጋራቱ የሚሰራበት ተቋም ጫና እንዳሳደረበት እና በራሱ ፈቃድ እንዲለቅ ግፊት ማድረጋቸውን ገልጿል።
“በራሴ ፈቃድ እንደለቀኩ የገለጽኩት በግፊት ነው “ያለው ሊንከር 26 አመት ካገለገለበት ቢቢሲ ሃሳቡን በመግለጹ ብቻ አስናብተውኛል ብሏል። የቀድሞው የባርሴሎና እና ሌስተር ሲቲ ተጫዋች ከኒውስ ወርልድ ጋር በነበረው ቆይታ በቢቢሲ ከፍተኛ ሃላፊዎች ውሳኔ ከስራው መሰናበቱን አረጋግጧል።
የ61 አመቱ ሊንከር በቀጣይ የውድድር አመት በኤፍ ኤ ካፕ የጨዋታ ትንተና እና በ2026ቱ አለም ዋንጫ በሌላ ሚዲያ ወደ ስራው እንደሚመለስ ተናግሯል።
በ-አልፈሪድ ነስሮ












