ሊጀመር በጣት የሚቆጠሩ ቀናት በቀሩት ተወዳጁ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ታላላቅ ቡድኖች ስብስባቸውን ለማጠናከር ውድ የሚባሉ ዝውውሮችን በመፈጸም ላይ ይገኛሉ።
ከፍተኛ ወጪ እየወጣ በላበት የዝውውር ገበያው ከዚህ ቀደሙ በተለየ መልኩ የእንግሊዝ ቡድኖች እስከዛሬ ካስመዘገቡትም በላይ ሪከርድ የሆነ ሂሳብ በዝውውር ገበያው ወጪ ሊያደርጉ እንደሚችሉ እየተዘገበ ይገኛል።
በተለምዶ TOP 6 በሚባሉ ቡድኖች በብዛት እየተፈጸሙ የሚገኙ ዝውውሮች አጥቂ እና የማጥቃት ሃይል የሚሆኑ ተጫዋቾች ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ለሚወጣው ወጪ መናር ዋነኛው መንስኤም ይህው መሆኑ ይገመታል።
የ9 ቁጥር አጥቂዎች በአለም እግርኳስ ላይ እየጠፋ መገኘት ዋጋቸውን ማስወደዱ ለአንድ ውድድር አመት ብቻ አስደናቂ ለሆኑ ተጫዋቾች የተጋነነ ሂሳብ ወጪ እንደሆን ምክንያት ሆኗል።
ሊቨርፑል፣ቼልሲ እና አርሰናል የ9 ቁጥር አጥቂ ችግራችንን ይቀርፋሉ በሚል በጥቅል 218 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ በማድረግ ሆጎ ኤኪቲኬ፣ ጆአው ፔድሮ እና ቪክቶር ዮኬሬሽን አስፈርመዋል።
በያዝነው የዝውውር ገበያ ሌላኛው የ9 ቁጥር አጥቂ ጥያቄ የሚነሳበት ማንችስተር ዩናይትድ ሁለት የፊት መስመር ተጫዋቾች ላይ ትኩረት ማድረጉን ለክለቡ ቅርበት ያላቸው የመገናኛ ብዙሃን እየዘገቡት ይገኛል። የአርቢ ላይብዚሹ ቤንጃሚን ሼሽኮ እና የአስቶን ቪላው ኦሊ ዋትኪንስ በቀያይ ሴይጣኖቹ በጥብቅ እየተፈለጉ ሲሆን ከሁለቱ አንዳቸውን ማስፈረሙ አይቀሬ መስሏል።
የአሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ቀዳሚ ምርጫ የሆነው ቤንጃሚን ሼሽኮ በኒውካስትል ዩናይትድ በጥብቅ እየተፈለገ መሆኑ ለዩናይትድ ስጋትን ደቅኗል። ተጫዋቹ ለሁለት የውድድር አመት በጀርመኑ ክለብ እያሳየ የሚገኘው ተደናቂ ብቃት በበርካታ የአውሮፓ ክለቦች ራዳር ውስጥ አስገብቶታል።
የሰሜን ለንደኑ አርሰናል የተጫዋቹ መዳረሻ ይሆናል በሚል ለወራት ቢዘገብም፣መድፈኞቹ ዮኬሬሽን ማስፈረማቸውን ተከትሎ ከዝውውሩ ወጥተዋል። ባለፉት ሳምንታት አሌክሳንደር ኢሳቅን የማጣት አደጋ ውስጥ የገባው ኒውካስትል ዩናይትድ ሼሽኮ ትክክለኛው ተተኪ እንደሚሆን በማመን ከላይብዚሽ ባለስልጣናት እና ከተጫዋቹ ወኮሎች ጋር ድርድር ጀምረዋል።
የ22 አመቱ ሼሽኮ ባሳለፍነው የውድድር አመት ቡድኑ የቻምፒዮንስ ሊግ ስፍራ ይዞ እንዲያጠናቅቅ ካስቻሉ ቁልፍ ተጫዋቾች አንዱ ሲሆን፣በ33 የቡንድስሊጋ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ 13 ግቦችን ከመረብ አሳርፏል። አርቢ ላይብዚሽ በተመሳሳይ በዚሁ ገበያ ሌላኛውን ወሳኝ ተጫዋቹን ዣቪ ሲሞንስ በቼልሲ ሊቀማ ከጫፍ በደረሰበት በአሁኑ ጊዜ ሼሽኮን የማቆየት ፍላጎት አለው ተብሏል።
የተጫዋቹ መውጣት የግድ ካለም እስከ 80 ሚሊዮን ዩሮ ማግኘት እንደሚፈልግ የጀርመን መገናኛ ብዙሃን ዘግበውታል።
ለማንችስተር ዩናይትድ ችግር የሚሆንበት ሼሽኮ የቻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎን የሚፈልግ መሆኑ ነው የሚለው አንድ ዘጋቢ፣ከዩናይትድ ይልቅ ወደ ኒውካስትል ሊያቀና የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
ሌላኛው የማንችስተር ዩናይድ ኢላማ እንግሊዛዊው ኦሊ ዋትኪንስ ወደ ቀያይ ሰይጣኖቹ የመጓዝ ዕድሉ ሰፊ ነው የሚለው ይሕው ዘጋቢ፣ፉክክር አልባ ዝውውር መሆኑ ተጫዋቹን በቀላሉ እንዲያገኙት ሊያደርጋቸው ይችላል ብሏል።
ዋትኪንስ ባሳለፍነው የውውድር አመት በጥር የዝውውር መስኮት አርሰናል ሊቀላቀል የነበረ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣አስቶን ቪላ ጆን ዱራንን በተመሳሳይ ጊዜ ማጣቱን ተከትሎ ዋትኪንስን ለመውሰድ መድፈኞቹ ያቀረቡትን የ20 ሚሊዮን ፓውንድ ጥያቄ ውድቅ አድርገውት ነበር።
አስቶን ቪላ የ29 አመቱን አጥቂ በጥሩ ሂሳብ ለመሸጥ የመጨረሻው የዝውውር ገበያ አሁን እንደሆነ በማመኑ ተጫዋቹን ለመሸጥ ፈቃደኛ እንደሆነ እየተዘገበ ይገኛል።
አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም በቡድን ስብስባቸው ባሉት ራስመስ ሆይሉንድ እና ጆሽዋ ዚርክዜይ ተማምነው አዲሱን የውድድር አመት ለመጀመር አይፈልጉም የተባለ ሲሆን የመጀመሪያ ምርጫቸው የማይሳካ ከሆነ ዋትኪንስ በቀጣዮቹ ጊዜያት የማንችስተር ዩናይትድ ንብረት መሆኑ የማይቀር መስሏል።
በ-አልፈሪድ ነስሮ












