የተወካዮች ምክር ቤት የገቢ ግብር ማሻሻያ አዋጅን በአምስት ተቃውሞ፣ በአሥራ ሁለት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አፅድቆታል፡፡
አዋጁ በስራ ላይ ረጅም አመታትን ያስቆጠረ በመሆኑ የንግዱን ውስብስብ ባህሪ ያማከለ ዘመናዊ የታክስ አሰባሰብ ስርዓት መዘርጋት አስፋላጊ ሆኖ መገኘቱን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ አብራርተዋል።
ማሻሻያው ከዲጂታል ኢኮኖሚው ጋር የተጣጣመ ዘመናዊ የታክስ መሰረት እንዲኖር ለማድረግና ለታክስ ማጭበርበር በር የሚከፍቱ አሰራሮችን ለመቀየር የሚያስችሉ ድንጋጌዎች መካተታቸውን ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡
የታክስ መሰረትን በማስፋት፣ የመንግስት ገቢ አሰባሰብን በማሻሻል እና የታክስ ፍትሐዊነትን በማረጋገጥ የመንግስትን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች በአዋጁ መካተታቸውን አቶ ደሰላኝ ጠቅሰዋል።
ማሻሻያው ምቹና ቀላል የታክስ ስርዓትን በመዘርጋት ለሀገራችን የተሻለ ኢኮኖሚ ለመፍጠር የሚያስችል እንደሆነም ጨምረው አስረድተዋል፡፡
የገቢ ግብር አዋጅ ማሻሻያ፣ ከግብር ነጻ የሆነው ከመቀጠር የሚገኘ ገቢ ከፍ እንዲል የተደረገ በመሆኑ ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ተቀጣሪዎች ላይ የግብር ጫናው እንደሚቀንስ፤ የግብር መሰረቱ እንዲሰፋ፤ መንግስት ከገቢ ግብር የሚያገኘው ገቢ በአንጻራዊ ሁኔታ ከፍ እንዲል አጋዥ መሆኑም በአዋጁ መመላከቱን ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡
አንዳንድ የምክር የገቢ ግብር ማሻሻያው የመንግስት ሠራተኛውን የኑሮ ሁኔታ ታሳቢ ያላደረገ ማሻሻያ በመሆኑ ምክር ቤቱ ማሻሻያውን በድጋሚ እንዲፈትሸው ጠይቀዋል፡፡
በማሻሻያው ላይ ከበርካታ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እንደተደረገበት እና እንደ ቋሚ ኮሚቴም ሰፊ ጊዜ ተወስዶበት የተዘጋጀ ማሻሻያ መሆኑም ነው የተገልጸው፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ማሻሻያው ለረጅም ጊዜ ውይይት እንደተደረገበት እና የሀገራት ልምድ እንደተወሰደ ጠቅሰው፣ ማሻሻያው ዘመኑን የዋጀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የመንግስት ሠራተኛውን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል፣ ከገቢ ግብር ማሻሻያ በተጨማሪ የመኖሪያ ቤት ጥናት እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡












