በ 2017 በጀት ዓመት ብልሹ አሰራሮችን ለማስቀረት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት እንደገለጹት ከፓስፖርት አገልግሎት ጋር ተያይዞ ብልሹ አሰራር ውስጥ የገቡ 26 ሰራተኞች በህግ ተጠያቂ ተደርገዋል ብለዋል።
አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ችግር የሚፈጥሩ ፣የማጭበርበርና የማታለል ተግባር የሚፈጽሙ እንዲሁም በህገወጥ መንገድ በኦንላይን አስቸካይ ፓስፖርት የሚሞሉ 231 ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ገልፀዋል።
3 ሺህ 868 ግለሰቦች የተጭበርበረ ሰነድ በመጠቀም ፓስፓርት ሊያወጡ ሲሞክሩ በህግ እንዲጠየቁ ተደርገዋል። ዳይሬክተሯ 12 ሺህ 127 የውጭ ዜጎች ሃሰተኛ ሰነዶችን በመያዝ በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ ተይዘው አስፈላጊውን እርምጃ እንደተወሰደባቸው ጠቁመዋል።
ከዚህ ውስጥ 3 ሺህ 263 የቪዛና ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ ሳያድሱ በህገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የውጭ ዜጎች የክፍያ መመሪያው በሚያዘው መሰረት አስፈላጊውን ውዝፍ ክፍያ ፈጽመው ከሀገር እንዲወጡ ተደርጓል ሲል የዘገበው ኢ ፕ ድ ነው።












