የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ዩክሬን ከቻለች ሞስኮን መምታት ትችላለች ብለዋል” በሚል ቢወቀሱም ሪፐብሊካኑ ግን አስተባብለዋል፡፡
ትራምፕ ለዘለንስኪ የነገሯቸው “ሞስኮን እንዳያጠቁ ነው” በሚል ዋይት ሃውስ ጭምር በጉዳዩ ላይ ማስተባበያ ሰቷል። ወደ ሩሲያ ጥልቅ ግዛት ዩክሬን ገብታ መምታት እንድትችል ትራምፕ ቮሎድሚር ዘለንስኪን በግላቸው አበረታተዋቸዋል የሚለው ሀሳብ ተቀባይነት የለውም ተብሏል፡፡
ፋይናንሻል ታይምስ ትራምፕ ዘለንስኪ ሞስኮን አሊያም ሴይንት ፒተርስበርግን በሚሳዔል እንዲመቱ በትራምፕ ተጠይቀዋል የሚል ዜና ይዞ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ ዘለንስኪም ያን ማድረግ እንደሚችሉ ምላሽ ለዶናልድ ትራምፕ ሰጥተዋል በሚል ጉዳዩ በመገናኛ ብዙሃን ሰፊ ሽፋን ተሰቶታል፡፡
ትራምፕ “ዘለንስኪ ሞስኮን ይመታሉ ወይ? “በሚል በጋዜጠኞች ሲጠየቁ ምላሻቸው “አይሆንም !ሞስኮን ዒላማ ውስጥ ማስገባት የለበትም፡፡” ሆኗል፡፡ የዋይት ሃውስ ፕረስ ሴክሬታሪ ካሮላይን ሊቪት ፋይናንሻል ታይምስ ያወጣውን ሀሳብም ተችተውታል፡፡
የሞተውን ጽሁፋቸውን ለማነቃቃት የትራምፕን የንግግር አውዶች ሳይረዱ ይጽፋሉ በሚል ወቅሰዋል ፕረስ ሴክሬታሪዋ፡፡ ዶናልድ ትራምፕ ሌት ተቀን የሚተጉት ንጹሃን እንዳይሞቱ እንጂ ጦርነትን ለማባባስ አይደለም የሚል ምላሽ የሰጡት ሊቪት የብሪታንያውን ጋዜጣ አጣጥለውታል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ አንዳንድ ሀሳቦች ውሸት እንደሚሆኑ ጠቁመው ሾልከው የሚወጡ ቁልፍ ሰነዶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ግን አጽንዖት ሰተውበታል፡፡
አር ቲ እንዳስነበበው።
በ-ቢኒያም ካሴ












