25ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ በኬንያ ናይሮቢ ተካሂዷል። ስብሰባውን የወቅቱ ሰብሳቢ እና የሶማሊያ የፋይናንስ ሚኒስትር ቢሂ ኢጌህና የአፍሪካ ልማት ባንክ የቀጣናዊ ትስስር፣ ልማት እና የንግድ ተደራሽነት ምክትል ፕሬዝዳንት ኔና ንዋቡፎ በጋራ መርተውታል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ባለስልጣን ምክትል ዋና ጸሐፊ መሐመድ አብዲ ዋሬ የቀጣናዊ ተቋሙን ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁን ወክለው በስበሰባው ተሳትፈዋል።
ሚኒስትሮቹ በቀጣናዊ ትስስር እና ልማት የተያዙ እቅዶችን የገመገሙ ሲሆን ትብብርን ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መክረዋል።
በቀጣናው ለኃይል ትስስር፣ ለማይበገር አቅም ግንባታ እና ለኢኮኖሚ ትስስር ፈሰስ የሚደረገውን የፋይናንስ መጠን ማሳደግ እንደሚገባም ተነስቷል።
ኢጋድ ቀጣናዊ ትስስር ለማጠናከር በማይናወጥ ቁርጠኝነት አበክሮ እንደሚሰራና አባል ሀገራት ዘላቂና ሁሉን አካታች እድገት እንዲያስመዘግቡ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ማስታወቁን ተገልጾል።
24ኛው የአፍሪካ ቀንድ ኢኒሼቲቭ የሚኒስትሮች ስብሰባ በሚያዚያ ወር 2017 ዓ.ም በዋሺንግተን ዲሲ ከዓለም ባንክ የፀደይ ወቅቶች ስብሰባ ጎን ለጎን መካሄዱ የሚታወስ ነው።
በወቅቱ ስብሰባ ኢትዮጵያ በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ ከየካቲት 2015 ዓ.ም አንስቶ በኢኒሼቲቩ የነበራትን የሰብሳቢነት ጊዜ አጠናቃ ለሶማሊያ አስረክባለች።
በአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የዓለም ባንክ እና አውሮፓ ሕብረት ድጋፍ የተቋቋመው ኢኒሼቲቭ ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር እንዲሁም በልማት ስራዎች በተለይም በመሰረተ ልማት፣ ንግድ፣ አቅም ግንባታ መስኮች የተሻሉ ውጤቶችን ማምጣት ዋነኛ የትኩረት አጀንዳ አድርጎ ይሰራል፡፡
በስብሰባው የኢኒሼቲቩ አባል ሀገራት የፋይናንስ ሚኒስትሮች፣ የጀርመን፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ የዓለም ባንክ፣ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡












