በቴክሳስ ውስጥ ባለፈው ሳምንት በተከሰተው ከባድ የጎርፍ አደጋ የሞቾች ቁጥር ከ120 ሲልቅ በርካቶች ደግሞ አሁንም የደረሱበት አልታወቀም፡፡ የጎርፍ አደጋው የበረታባቸው የግዛቱ ነዋሪዎች እራሳቸውን ለማዳን እየወሰዱት ያለው አማራጭ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል፡፡

ከልጅ እስከ አዋቂ እራሳቸውን ለማዳን ዛፎች እና ፍርስራሾችን መያዝ እንደአማራጭ መጠቀም መጀመራቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡ ዜጎቹ የነብስ አድን ሰራተኞች እስኪ ደርሱላቸው ድረስ ለሰዓታት አለፍ ካለም ለአንድ ሙሉ ቀን ዛፎችን፣ ቅርንጫፎችን እንዲሁም የፍርስራሽ ቁርጥራጮችን አጥብቀው በመያዝ እራሳቸውን ከከፋው የጎርፍ አደጋ ለማዳን ጥረት ማድረጋቸው ተዘግቧል፡፡
ሌላኛው ደግሞ ነዋሪዎች እራሳቸውን ለማዳን የወሰዱት አማራጭ በየቤታቸው ጣሪያ ላይ መውጣትን ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የጎርፉ መጠን በ45 ደቂቃ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት 26 ጫማ አልያም 8 ሜትር ከፍ በማለቱ ነው፡፡ መኖሪያ ቤቶቹ በጎርፍ ሲጥለቀለቁ የበርካቶች ማምለጫ መንገድ የነበረው በቤታቸው ሰገነት ላይ መውጣት ብቻ ነበር፡፡ በዚህም የአንድ ቤተሰብ ታሪክ የብዙዎችን ልብ የነካ እና ቀልብ የሳበ ነበር፡፡
ብራይደን እና ብሮክ ዴቪስ የተባሉ ወንድማማቾች በቤታቸው ጣሪያ ላይ መውጣት እራሳቸውን ከሞት ታድገዋል፡፡ የ9 ዓመቱ ብራይደን እና የ7 ዓመቱ ብሮክ፣ በጓዳ-ሉፔ ወንዝ አቅራቢያ በሚገኘው ካምፕ ላ ሁንታ ውስጥ እያሉ ነበር የጎርፈ አደጋው የደረሰው፡፡
ብራይደን “ምን እየተካሄደ እንዳለ በትክክል አላውቅም ነበር” ቢልም፣ ታናሽ ወንድሙ ብሮክ ግን ከእንቅልፉ ሲነቃ ቤታቸው በጎርፍ ተጥለቅልቆ እንደነበር በመረዳት ወዲያውኑ ወደ ጣሪያው ሊያመራ ችሏል፡፡ በዚህም የእራሱን እና የወንድሙን ህይወት ከጎርፍ አደጋው ታድጓል፡፡
እናታቸው ኬሊ ራቦን፣ ልጇ እንዴት እንዳመለጠ ስትገልጽ “ይህ በጣም ከባድ እና በልጅነት አእምሮ ሊታሰብ የሚችል ውሳኔ አይደለም ስትል ተናግራለች፡፡
ከዚህም ባለፈ ነዋሪዎች በጊዜያዊ መንገድ ከአደጋው ሊያርፋቸው የሚችሉበትን ማንኛውም መንገድ ሲጠቀሙ ቆይተዋል፡፡ አንዳንዶች በድፍረት እየዋኙ ከፍታ ወዳለው ስፍራ ለመጓዝ ጥረት ሲያደርጉ ሌሎች ደግሞ በጎርፉ ላይ ለመንሳፈፍ የሚረዳቸውን ማንኛውንም ተንሳፋፊ ነገርን በመያዝ በጊዜአዊነት እራሳቸውን ለማዳን መሞከራቸው ተገልጾል፡፡
እራሳቸውን በተለያዩ መንገድ ለማትረፍ ጥረት ያደረጉ ዜጎችን ለመታደግ ሄሊኮፕተሮች በስፋት በስፍራው ተሰማርተዋል፡፡ በጣሪያዎች፣ በዛፎች ላይ እና በከባድ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ዜጎችን በሄሊኮፕተሮች አማካኝነት ህይወታቸውን መታደግ መቻሉን ተመላክቷል፡፡
በቴክሳስ የየጎርፍ አደጋ በነፍስ አድን ስራዎች አስደናቂ ጥረት የታየበት እንደሆነ ብዙዎች እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች፣ የፌደራል እና የግዛት ኤጀንሲዎች እንዲሁም በርካታ በጎ ፈቃደኞችን ጨምሮ፣ ከፍተኛ የፍለጋ እና የነፍስ አድን ስራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትራምፕን ጨምሮ የግዛቱ ባለስልጣናት የጎርፍ አደጋው “የ100 ዓመት አደጋ” ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡ ይህም አልፎ አልፎ የሚከሰት እና አጥፊነቱ የከፋ አደጋ ስለመሆኑ አመላካች ነው ተብሏል፡፡
ከአደጋው በህይወት የተረፉ ሰዎች በሌሊት የተከሰተውን የጎርፍ አደጋ እና የነበረውን ፍጥነት ለመግለፅ ክስቱትን “ጥቁር የሞት ግድግዳ” በማለት ገልፀውታል፡፡
በ ሀሴት ሀይሉ












