ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚችሉ የልማት ስራዎችን እየሰራች ቢሆንም ዓለም አቀፍ እገዛ ያስፈልጋታል ተባለ።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሕብረት ጋር በመተባበር ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ለማስተናገድ ቅድመ ዝግጅት እያደረገች ነው። ጉባኤውን አስመልክቶ የፕላንና ልማት ሚንስቴር ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ካደረጉት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኤጄንሲዎች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።

በውይይቱም አፍሪካ እንደ አህጉር የአየር ንብረት ለውጡ ምርት እና ምርታማነትቷን እየጎዳ እንደሆነ ተመላክቷል። የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግ በጽኑ ታምናለች ብለዋል።
ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ አስፈላጊ ዝግጅት መደረጉን ገልፀው፤ አየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የጋራ ሀሳቦች የሚያዝበት ይሆናል ብለዋል።
ጉባኤው አፍሪካን የሚመራ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ከፍ ማድረግ አለበት ፤ ለምንድነው አፍሪካ ለአየር ንብረት መፍትሄ የሚገባውን እውቅና እና ድጋፍ ያላገኘችው? የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት የአፍሪካን እውነታዎች እና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች እንዴት በተሻለ ሁኔታ ሊያንፀባርቅ ይችላል? የሚሉ ወስኝ ጥያቄዎች መነሳት እንዳለባቸው ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚችሉ የልማት ስራዎችን እየሰራች መሆኑን የገለፁት ሚኒሰትሯ፣ ዓለም አቀፍ እገዛ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጡ ችግሮችን ለመቋቋም የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብርን አጠናክራ ትቀጥላለች። እንዲሁም በዘላቂነት ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ስምምነቶችን ተግባራዊ እያደረገች መሆኑን አንስተዋል።
”የአረንጓዴ ጉዳይ ውይይቶች አረንጓዴነትን ማዕከል ያደረጉ ርምጃዎች” በሚል መሪ ቃል ከጳጉሜ 03-05/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል የሚስተናገደው ጉባኤው፣ አፍሪካውያን ስለ አየር ንብረት ለውጡ የሚመክሩበት እና ለቀጣይ የኮፕ 30 ዓለም አቀፍ ጉባኤ በአየር ንብረት ለውጡ ዙሪያ አፍሪካ እየደረሰባት ያለውን ችግር በግልፅ የሚያሳይ እና አፍሪካዊያን የሚገባቸውን የሚጠይቁበት እንደሆነ ተገልጾል፡፡
በ ሔርሜላ ፍቃደ












