July 5, 2025
የኢፌዴሪ ባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በመቀናጀት “ስፖርት ለአሸናፊ ሀገር” በሚል መሪ ቃል የፓናል ውይይት በመካሄድ ላይ ይገኛል። በውይይት መድረኩ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት በባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ መኪዩ መሐመድ፣ አዲስ የተሻሻለ የስፖርት ፖሊሲ ተግባራዊ ሊደረግ በሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

እስካሁን በስራ ላይ የዋለው በ1990 በኢሕአዴግ መንግሥት ተግባራዊ የሆነው ፖሊሲ ነው ያሉ ሲሆን፣ ስፖርትን እንደ መዝናኛ ብቻ ይመለከት የነበረ ነው ብለዋል። ስፖርት ላይ ያሉ ማነቆዎች በዋነኝነት ሶስት ናቸው ያሉት አቶ መኪዩ የተቋማት ቅንጅት አለመኖር፣ የስልጠና ማዕከላት መዋቅራዊ ስብራት እና የፖሊሲ ስብራት ናቸው ብለዋል።
መንግሥት ዘርፉን በሚመለከት የዕይታ ለውጥ እንዲመጣ ከፍተኛ ስራ ሰርቷል ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው፣ በካቢኔ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶ ውይይት መደረጉን አንስተዋል። አያይዘውም ፖሊሲ ከመቅረፅ በላይ ተግባራዊ ማድረግ ላይ ያሉ ክፍተቶችን መቅረፍ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የፓናል ውይይቱ እንደቀጠለ ይገኛል።
በ-አልፈሪድ ነስሮ (ከ ባሕርዳር)












