ከህንድ አህመዳባድ ወደ ለንደን ጋትዊክ ትላንት ሐሙስ ሰኔ 12/ 2025 ሲበር የነበረው አውሮፕላን ተነስቶ ብዙም ሳይቆይ አደጋ ደርሶበታል።
ቦይንግ 787-8 ድሪምላይነር አውሮፕላኑ 242 ሰዎችን (230 ተሳፋሪዎችን እና 12 የበረራ ሰራተኞችን) ጭኖ የህክምና ኮሌጅ ሆስቴል እና የመኖሪያ አካባቢ ውስጥ ወድቋል። በዚህም በአውሮፕላኑ ውስጥ ከነበሩት 241ዱ ህይወታቸው ሲያልፍ፣ አደጋው የደረሰበት አካባቢም በርካታ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል ተብሏል። ከአውሮፕላኑ ተሳፋሪዎ አንድ ተሳፋሪ ብቻ ከአደጋው ተርፏል።
ከዚህ አደጋ ጋር በተያያዘ የአንድ ቤተሰብ ልብ የሚሰብር እና አሳዛኝ ታሪክ እነሆ፡-
ከአደጋው በኋላ ከታዩት እጅግ በጣም አሳዛኝ ታሪኮች አንዱ የራጃስታን የጆሺ-ቪያስ ቤተሰብ ነው። ዶ/ር ካኡሚ ቪያስ፣ ባለቤቷ ፕራቲክ ጆሺ እና ሦስት ልጆቻቸው፦ ሚራያ፣ ፕራድዩት እና ናኩል (መንትዮች) በዚያ በረራ ላይ ነበሩ። ዶ/ር ፕራቲክ ጆሺ በለንደን ለስድስት ዓመታት ስኬታማ የህክምና ስራን ገንብቷል። ህልሙም ባለቤቱን ዶ/ር ኮሚ ቪያስን እና ሶስት ልጆቻቸውን (የስምንት ዓመቷ ሚራያ እና የአምስት ዓመት መንትያ ልጆቻቸው ፕራድዩት እና ናኩል) በመጨረሻ ወደ እሱ ማምጣት፣ አዲስ የህይወት ምዕራፍ መጀመር ነበር።
ዶ/ር ኮሚ እራሷ በኡዳይፑር በሚገኘው ፓሲፊክ ሆስፒታል ሀኪም ስትሆን፣ ከባለቤቷ ጋር ለመገናኘት እና ልጆቻቸውን በለንደን አንድ ላይ ለማሳደግ ባላት ከፍተኛ ጉጉት ከስራዋ በቅርቡ ነበር የለቀቀችው።
ሐሙስ፣ ሰኔ 12፣ 2025፣ የጆሺ-ቪያስ ቤተሰብ ቦይንግ 787-8 ድሪምላይነርን ተሳፈሩ። በአውሮፕላኑ ውስጥ ያለው ድባብ በተስፋ እና በደስታ የተሞላ ነበር ። ከአደጋው ጥቂት ደቂቃዎች በፊት ፕራቲክ ጆሺ መላውን ቤተሰብ በአውሮፕላኑ ውስጥ ሆኖ ሴልፊ ፎቶ አንስቷል። ፎቶው ንጹህ እና ያልተበረዘ ደስታን ያሳያል፣ በአዲስ ህይወታቸው ተስፋ የተሞሉ ነበሩ።
ፕራቲክ እና ኮሚ ጎን ለጎን ተቀምጠዋል፣ ልጆቻቸው ሚራያ፣ ፕራድዩት እና ናኩል ከወዲያኛው መቀጫ ካሜራውን እየተመለከቱ፣ አይኖቻቸው በወጣትነት ጉጉት ያበራሉ።
ቤተሰቡ ይህንን አዲስ ጉዞ ለመጀመር እያሰበ ነበር፣ ግን በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ሁሉም በአደጋው ሞተዋል።
የአደጋው መንስኤ ምርመራ በመካሄድ ላይ ሲሆን፣ ባለሙያዎች እንደ ድንገተኛ የኃይል መጥፋት፣ የኮምፕረሰር ብልሽት ወይም የአእዋፍ ግጭት የመሳሰሉ ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎችን እየመረመሩ ነው። የአውሮፕላኑ ጥቁር ሣጥን ተገኝቷል፣ ይህም ትክክለኛውን መንስኤ ለማወቅ ወሳኝ ይሆናል።
በ- ሃና ተሰማ












