::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::::
የትምህርት ተደራሽነት እና ጥራትን ለማረጋገጥ በቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የትምህርት ዘርፉን በቴክኖሎጂ ለማዘመን ያለመ የቴክኖሎጂ ፎረም ሪች ፎር ቼንጂ ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽንና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን፤ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቀጥል ይሆናል፡፡
በሚኒስትር ዲኤታ ማዕርግ የትምህርት ሚኒስትር አማካሪ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት፤ የትምህርት ስርዓቱን ማዘመን ከሀገራዊ የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል። መድረኩ በትምህርት ዘርፉ ለሚስተዋሉ ክፍተቶች በቴክኖሎጂ የተደገፈ መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችሉ እሳቤዎች የሚገኙበት ነው፡፡

የማስተርካርድ ፋውንዴሽን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ስርአት የትምህርት ማእቀፉን በአዳዲስ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች በማስደገፍ ለችግሮች ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ የመማር ማስተማር ሂደትን የሚያፋጥን መድረክ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡ የሪች ፎር ቼንጂ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር መቅድም ጉልላትም በበኩላቸው ቴክኖሎጂን በመጠቀም የትምህርት ስርዓቱን መደገፍ መሰረታዊ ስለመሆኑ አመላክተዋል፡፡

የዲጂታል የትምህርት ስርአቱን የሚያዘምኑ 11 የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች ተደራጅተው ትምህርት ማእቀፉን ለማዘመን እረጂ ስለመሆናቸው ተነግሯል፡፡
የትምህርት ተደራሽነት እና ጥራትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ጥረት የቴክኖሎጂ ሚና የጎላ ሲሆን 50 የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ስርዓቱን በቴክኖሎጂ የማስደገፍና የዲጂታል ቤተ-መጻሕፍትን የማስፋፋት ስራ ላይ እየሰሩ ስለመሆኑ ተመላክቷል በፎረሙ ስራ ፈጣሪዎች፣ፖሊሲ አውጪዎች፣ የትምህርት ዘርፉ ተዋንያን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
በ-ማህሌት ግርማ












