በ – ሰላም ይልማ
“ስለ ኢትዮጵያ” የተሰኘውና በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሚዘጋጀው የምዕራፍ ሁለት አካል የሆነውን የስራ ዕድል ፈጠራ መድረክ እየተካሄደ ነው።

ለተሳታፊዎቹ መልክታቸውን በቪዲዮ ያጋሩት የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈርያት ካሚል፣ መድረኩ በስራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚንቀሳቀሱ ባለድርሻ አካላትን ያቀናጀ በመሆኑ እንደ አገር ዘርፉ ላይ መስራት ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
የስራ ዕድል ፈጠራ ስራ አጥ የሆኑ ዜጎች በጥቃቅንና አነስተኛ አደራጅቶ የዕለት ጉርስን ከመሸፈን እሳቤ ባሻገር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግናን የሚያረጋግጥ የስራ ዕድል ፈጠራ በማተኮር ሀብትን ለማፍራት የሚያግዝ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ዘርፉን ለማሳደግ የሁሉንም ቅንጅት የሚጠይቅ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ ዜጎች ክህሎት መር የሆነ አቅም ሊኖራቸው እንደሚገባ በማንሳት በሚኒስቴሩም በኩል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዘርፉን ለማሳደግ የፋይናንስ ትስስር ማጠናከር፣ የግል ዘርፉን የነቃ ተሳትፎ ማሳደግ እና ክህሎት መር እቅምን ማጎልበት እንደሚገባ በመድረኩ ተጠቁሟል።የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በምዕራፍ አንድ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ መድረኮች ተዘጋጅቶ ነበር። ምዕራፍ ሁለት ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ መድረክን እያካሄደ ይገኛል።
የዛሬው መድረክ የስራ ዕድል ፈጠራ ውይይት በአዳማ እየተካሄደ ሲሆን፣ ስኬቶችና ችግሮች ላይ በመምከር በቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተመከረበት ነው። በዘርፉ ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይትም እየተካሄደ ነው።