፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡
የአካባቢ ብክለትን መከላከል የሚያስችለው ሁለተኛው ዙር የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ማስጀመርያ መርሐግብር ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።
መርሐ ግብሩ “ከዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀን” ጋር በማስተሳሰር ነው በመካሄድ የሚገኘው።
በመርሐግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት፥ የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ለሊሴ ነሜ፥ የፕላስቲክ፣የአየር፣ የውሃ፣የአፈርና የድምጽ ብክለትን መከላከል ቅንጦት ሳይሆን መሰረታዊ መብት ነው ብለዋል።
ዜጎች ጤናማ አካባቢ የመኖር ህገ-መንግስታዊ መብት እንዳላቸው የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሯ፥ ለዚህም ጽዱ ኢትዩጵያን ለመፍጠር አልሞ የተጀመረው የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ አስፈላጊነትን አንስተዋል።
በመጀመሪያው ዙር የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ የፕላስቲክ፣የአየር፣ የውሃ፣የአፈርና የድምጽ ብክለትን መከላከል እንዲሁም የአካባቢና ማህበራዊ ተጽዕኖ ሰነዶች ግምገማ መድረክ መካሄዱን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሯ፥ የሁለተኛው ዙር የጽዱ ኢትዩጵያ ንቅናቄም ይህን በማጠንከር ይቀጥላል ብለዋል።
በመጀመሪያው ዙር ጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ከ7.3 ሚሊየን በላይ ዜጎች ተሳታፊ ማድረግ መቻሉን ገልጸው፥ በዚህም ዜጎች ጽዳትና የአካባቢ ጥበቃ ስራን ባህል እንዲያደርጉ ግንዛቤ ተፈጥሯል ብለዋል።
በሁለተኛው ዙር የጽዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄም ጽዳትና የአካባቢ ጥበቃ ስራን ባህል ማድረግ በሚያስችል መልኩ በርካታ ስራዎች የሚሰሩበት እንደሆነ ገልጸው፥የችግኝ ተከላ እና መንከባከብ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሥራዎችም የሚከናወኑበት ይሆናል ብለዋል።
መርሀግብሩ ለስድስት ተከታታይ ወራት በተለያዩ የአየር ብክለትን እና የአካባቢ ጤናን ጥበቃን ለማረጋገጥ አጋዥ በሆኑ ስራዎች እንደሚካሄድ ተገልጿል።
በ- ሰላማዊት ወንድወሰን












