ሙሉ መልዕክት እንሆ ![]()
እንኳን ለ1ሺህ 446ኛው የአረፋ ( ዒድ አል አድሃ ) በዓል አደረሣችሁ! አደረሠን ሲል የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአረፋ በዓልን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክት ለሕዝበ ሙስሊሙ አስተላልፏል።

አረፋ የመታዘዝና የመስዋዕትነት በዓል ነው፤ ነብዩ ኢብራሂም ለታላቅ ክብር የበቁት የተጠየቁትን መስዋዕትነት ለመክፈል በመታዘዛቸው ነው። ነብዩ ኢብራሒም ልጃቸው ኢስማኤልን ለመሰዋት ልባዊ ዝግጅት አድርገዋል፤ አላህ የነብዩን እውነተኝነት አይቶ በምትኩ የሚሰዋውን በግ ልኮላቸዋል። ስለሆነም ነብዩ ኢብራሒም በከፈሉት መስዋዕትነት ድል አድርገው ክብርና በረከትን ከአላህ ዘንድ አግኝተዋል ።
ይህ ሐይማኖታዊ አስተምህሮ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። እምነት ላይ ፅናትና መስዋዕትነት እንዳለው ሁሉ ስለሀገርም ፅናትና መስዋዕትነት ይጠይቃል።
ኢትዮጵያ ፀንታ የቆየችው በየዘመናቱ የነበሩ ጀግኖች ልጆቿ በከፈሉት መስዋዕትነት ነው፤ ኢትዮጵያ በአሁን ወቅት የልጆቿን መስዋዕትነት ትጠይቃለች ያለው ምክር ቤቱ ፤ ይህም ጠንክሮ በመሥራት ድህነትንና ኋላቀርነትን አሽቀንጥሮ ለመጣልና በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታችንን በማረጋገጥ በየሥራ መስካችን በመረባረብ ሀገራዊ ዕመርታ ማምጣት አለብን።
ይህም በመሆኑ ለሀገራችን ሠላም፣ ልማትና ብልፅግና ሊኖረን የሚገባው ፅናትና መስዋዕትነት ከዚሁ በዓል የምንማረው ትልቅ ትምህርት ነው ሲል ባስተላለፈው መልዕክት ገልጿል።
ቀጣዩ ትውልድ በብልፅግና እንዲኖርና የኢትዮጵያን ገናናነት ለመመለስ የአሁኑ ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነቱን ለአፍታም ያህል መዘንጋት የለበትም ያለው ምክር ቤቱ ወቅቱ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ በመሆን ብዝሐ ታታሪነትን በሁሉም መስክ በማስፋት፣ ለተጨማሪ ስኬት ተግተን በመሥራት የሀገራችንን ሁለንተናዊ ብልፅግና ማረጋገጥ ይኖርብናል ሲል ገልጿል።
ከጥላቻ ይልቅ ለፍቅር፣ ከመገፋፋት ይልቅ ለአብሮነትና መቻቻል ፣ከብሽሽቅ ፓለቲካ ይልቅ ለምክክርና ለውይይት ልባችንን ክፍት ልናደርግና የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ሲል ምክር ቤቱ ባስተላለፈው መልዕክት ገልጿል።
አክሎም በምክንያት ላይ የተመሠረተ የሰለጠነ የፓለቲካ ባህል በማራመድ ለኢትዮጵያ ሠላምና የግዛት አንድነት መፅናት ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ በዚህ አጋጣሚ ምክር ቤቱ መልዕክት አስተላልፏል።












