በኢትዮጵያ የጡት ካንሰር ከሌሎች የካንሰር አይነቶች ቀዳሚ ሲሆን ይህ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል፡፡ ከጠቅላላው የካንሰር ተጠቂዎች 33% የጡት ካንሰር ቢሆንም፣ የጡት ካንሰር በቅድመ ምርመራ በሚደረግበት ወቅት የመዳን እድሉ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ብሩህ ተስፋ ነው።
የቅድመ ምርመራ !
📌 የጤና ባለሙያዎች አበክረው እንደሚናገሩት፣ የጡት ካንሰር በቶሎ ከተገኘ የመዳን እድሉ ከፍተኛ ነው። ይህ ማለት፣ በሽታውን ገና በለጋ ደረጃ ላይ መለየት ከቻልን ህይወትን ማዳን እንችላለን። ምንም እንኳን የጡት ካንሰር መጀመሪያ ላይ ህመም ባይኖረውም፣ ሴቶች በየወሩ የራሳቸውን ጡት በመመርመር ወይም እድሜያቸው ከ35 ዓመት በላይ ከሆነ በየዓመቱ የህክምና ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው ይመከራል። ይህ ቀላል እና ወሳኝ እርምጃ የብዙዎችን ህይወት ሊታደግ ይችላል።
ወንዶችም የጡት ካንሰር ተጠቂ ሊሆኑ ይችላሉ
📌ምንም እንኳን የጡት ካንሰር በብዛት በሴቶች ላይ የሚከሰት ቢሆንም፣ ወንዶችም ሊጠቁ እንደሚችሉ መዘንጋት የለብንም። የጡት ካንሰር ከ0.5% – 1% የሚሆነው በወንዶች ላይ እንደሚከሰት ይገመታል። ይህ የሚያሳየው ወንዶችም ቢሆኑ ምልክቶችን ካዩ ወይም የቤተሰብ ታሪክ ካላቸው ንቁ መሆን እና የህክምና እርዳታ መፈለግ እንዳለባቸው ይነገራል።
ልንለውጣቸው የምንችላቸው አጋላጭ ሁኔታዎች
📌የጡት ካንሰር አጋላጭ ሁኔታዎች በሁለት ይከፈላሉ። ሊለወጡ የማይችሉ እና ሊለወጡ የሚችሉ። ሊቀየሩ የማይችሉ አጋላጭ ሁኔታዎች ላይ ቁጥጥር ባይኖረንም (እንደ እድሜ፣ ጾታ፣ ዘረመል፣ እና የወር አበባ ዑደት)፣ ሊለወጡ የሚችሉትን በመቀየር
የበሽታውን ስጋት በእጅጉ መቀነስ እንችላለን!
📌ክብደት መጨመር/ውፍረት: በተለይም ከወር አበባ ማረጥ በኋላ የሚከሰት ውፍረትን በመቀነስ ለጡት ካንሰር የመጋለጥ እድልን መቀነስ ይቻላል።
📌አልኮል መጠጥ: ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣትን ማስወገድ ወይም መቀነስ አደጋውን ይቀንሳል።
📌የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ: የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ለጡት ካንሰር ተጋላጭነትን ለመቀነስ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
📌ትምባሆ: ማጨስን ማቆም ለተለያዩ የካንሰር አይነቶች የመጋለጥ እድልን በእጅጉ ይቀንሳል።
📌የሆርሞን መድሃኒቶች: የሆርሞን መድሃኒቶችን ከመጠቀምዎ በፊት ከሀኪም ጋር መነጋገር እና አማራጮችን መመርመር አስፈላጊ ነው።
የጡት ካንሰር ምልክቶችን ማወቅ እና ፈጣን ምላሽ መስጠት
📌ምልክቶችን አስቀድሞ ማወቅ ለቅድመ ምርመራ ወሳኝ ነው። የሚከተሉት ምልክቶች ከታዩ ወዲያውኑ የህክምና እርዳታ ማግኘት የህይወት አድን ሊሆን ይችላል።
📌በጡት ወይም በብብት አካባቢ የሚፈጠር እብጠት: አብዛኛዎቹ እብጠቶች ካንሰር ባይሆኑም፣ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
📌በቆዳ ላይ የሚታይ የቀለም ለውጥ
📌የጡት ጫፍ ወደ ውስጥ መሰርጎድ ወይም ቁስለት
📌ከጡት ጫፍ የሚወጣ የተለየ ፈሳሽ
📌ያልተለመደ የጡት ህመም (በተለይም የወር አበባ በሌለበት ጊዜ የሚቀጥል)
📌ሳል ወይም የጀርባ ህመም (ካንሰሩ ወደ ሌሎች የሰውነት ክፍሎች መሰራጨቱን ሊያመለክት ይችላል)
በ- ሃና ተሰማ
ማስፈንጠሪያውን (ሊንኩን) በመጫን NBC ኢትዮጵያን ይጎብኙ ይወዳጁ
👇👇👇👇👇👇👇
https://linktr.ee/NBCEthiopiaTV












