:::::::::::::::::::::::::::::::
ባለፉት ሶስት አመታት በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ሲያከናውን የቆየው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የፌደራል የባለ ድርሻ አካላት የምክክር መድረክና የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ ሂደት በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ ማስጀመሪያ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕ/ር መስፍን አርአያ ችግሮቻችንን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ባለ መቻላችን በርካታ መስዋዕትነቶችን አስከፍሎናል ብለዋል።
በእስካሁኑ የሀገራዊ ምክክር ሂደት እየተሳተፉ የሚገኙ በርካታ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ቢኖሩም አሁንም ድረስ ወደ ሂደቱ ያልገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሂደቱ እንዲገቡ የጠየቁ ሲሆን በኮሚሽኑ ላይ ያሉ ችግሮችንም ካሉ ለማስተካከል ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤን ጨምሮ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎችና የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ተገኝተዋል።
ዛሬን ጨምሮ እስከ ግንቦት 24 የሚቆየው የፌደራል የባለ ድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የምክክር ምዕራፍ በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ የሚከናወን መሆኑ ተገልጿል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ተሳታፊዎች ለሰባት ቡድኖች በመከፈል አጀንዳቸውን የሚያደራጁ ሲሆን በሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ በሰባት ቡድኖች የተሰበሰበውን አጀንዳ በማጠናቀር የፌደራል ተቋማትና ተሳታፊዎች አጀንዳ በሚል ለኮሚሽኑ ርክክብ በማድረግ ይጠናቀቃል።
በ – አክረም ኑርያ












