፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡
የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር መስሪያ ቤት አመራሮችና ሠራተኞች “የመሐል ዘመን” በሚል ርእስ በተዘጋጀዉ ሀገራዊ ሰነድ ላይ ውይይት አካሔዱ።
የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) እንደገለፁት ተቋማት እና ግለሰቦች የተጣለባቸዉን ኃላፊነት በብቃት፣ በጥራትና ወቅቱ በሚጠይቀው አግባብ መወጣት ከቻሉ የኢትዮጵያ የብልጽግና ሕልሞች የሚሳኩ ለመሆናቸው ያለፉት ዓመታት ስኬቶች ምስክር መሆናቸውን ገልጸዋል ።
የመሐል ዘመን በሚል ርእስ የተዘጋጀውን የመወያያ ሰነዱን የአገልግሎቱ ሚኒስትር ድኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ያቀረቡ ሲሆን ኢትዮጵያ ባለፉት 7 ዓመታት በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ከነበረችበት ሁኔታ መሰረታዊ በሆነ መልኩ እድገት ያስመዘገበች መሆኑን በመጥቀስ፤ ይህንን ለውጥ ወደፊት ለማስቀጠልና ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ ለማድረስ በውስጥና በውጭ ያሉ ክፍተቶችንና ተጋላጭነቶችን ነቅሶ በማውጣት መስራት እንደሚገባ አስታውቀዋል።

“ሃገራችን በለውጥ ሂደት ያለፈችው የለውጡን ቀልባሽ ኃይሎች በመርታት ብቻ አይደለም፤ በርካታ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሠራሽ ፈተናዎችን ጭምር በመሻገር እንጅ” ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።
የሕዝብን ጥያቄዎች በመመለስ፣ አካታች የፖለቲካ ሥርዐት በመዘርጋት፣ የኢኮኖሚ ሪፎርም በማድረግና ዕድገቱን በማስቀጠል፣ የትርክት ለውጥ በማድረግና ፈተናዎችን በመቋቋም በርካታ ስኬቶች በየዘርፉ መመዝገባቸውን አቶ ተስፋሁን ገልጸዋል።
ይሁን እንጅ እነዚህ ስኬቶች የፈጠሩት መለስተኛ እርካታ ወደማይቀለበሰው የብልጽግና መዳረሻ የሚደረገዉን ጉዞ እንዳያሰናክሉ በብስለት ማለፍ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ለዚህም በስኬቶች ሊደበቁ የሚችሉ ውስጣዊ ክፍተቶችን ያለማቅማማት መፍታት እንደሚገባ መጥቀሳቸውን ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በውይይቱ የተሳፉት የአገልግሎቱ አመራር እና ባለሙያዎች ሰነዱ በርካታ ጉዳዮችን የዳሰሰና ተጨባጭ ሁኔታዉን ያገናዘበ መሆኑን ገልጸው፤ ሀገራዊ የለውጥ ጉዞዉ ያለበትን ደረጃና ቀጣይ የሚጠይቀውን ጥረት በእጅጉ እንደተረዱበት ተናግረዋል።












