።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ በፓርክ ደ ፕሪንስ ፒኤስዤ ከአርሰናል ምሽት 4 ሰዓት ይጨወታሉ።
በኤምሬትስ በተደረገው የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ የፓሪሱ ቡድን 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት ማሸነፉ የምሽቱን ፍልሚያ ተጠባቂ አድርጎታል።
ከጨዋታው አስቀድሞ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ የመድፈኞቹ የአማካኝ መስመር ተጫዋች ዴክላን ራይስ ውጤቱን ለመልቀልበስ “ተዓምራዊ አጋጣሚዎች ያስፈልጉናል” ሲል ተደምጧል።

አያይዞም “ ከቻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ 90 ደቂቃ ርቀት ላይ መገኘታችንን መረዳት ያስፈልገናል፣ ይህ በራሱ በሜዳው ውስጥ ያለንን አቅም አሟጠን ለመጠቀም ብርታት ሊሆነን ይገባል” በማለት ተናግሯል።
እንግሊዛዊው ተጫዋች አርሰናል በሩብ ፍጻሜው ሪያል ማድሪድን በጣለበት ጨዋታ በደርሶ መልስ ድንቅ አቋሙን ማሳየቱ እና ሁለት ውብ የቅጣት ምት ጎሎች ማስቆጠሩ አይዘነጋም።
ከፒኤስዤ ጋር በነበራቸው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ቶማስ ፓርቴ በቅጣት ባለመሰለፉ የተካላካይ አማካኝነት ስፍራን ይዞ መጫወቱ ይታወሳል።
በዛሬው ጨዋታ ጋናዊው ፓርቴ ወደ አሰላለፍ የሚመለስ በመሆኑ፣ ራይስ ይበልጥ ወደ ፊት በመጠጋት የመድፈኞቹን የአጥቂ መስመር ያግዛል ተብሎ ይጠበቃል።
አርሰናል በምሽቱ ጨዋታ አሸንፎ ወደ ፍጻሜ ማለፍ ከቻለ ከአውሮፓውያኑ 2006 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል።
በ- አልፈሪድ ነስሮ












