NBC Ethiopia በ – ቢኒያም ካሴ
April 28, 2025
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የ72 ሰዓታት ተኩስ አቁም አወጁ፡፡ ፑቲን ተኩስ አቁም አዋጁን ይፋ ያደረጉት ሶቭየት ህብረት በናዚ ጀርመን ላይ ድል የተቀዳጀችበትን 80ኛ ዓመት በማስመልከት ነው፡፡

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ናዚ ድል የተደረገበትን 80ኛ ዓመት ግምት ውስጥ አስገብተው ለሰባ ሁለት ሰዓታት ተኩስ አቁም ይፋ ያደረጉት ፑቲን ለሰላም በር እየከፈቱ ነው የሚል አረዳድ እንዲኖርም አድርገዋል ፡፡
ክሬሚሊን እንዳሳወቀው ከፈረንጆቹ ግንቦት 8 እስከ 10 የሚቆይም ይሆናል ተኩስ አቁሙ ከግንቦት ሰባት እኩለ ሌሊት ጀምሮ ገቢራዊ የሚደረግ ሲሆን ምንም ዓይነት ጥቃት በዩክሬን ኃይሎች ላይ አይሰነዘርም ተብሏል ፡፡
ሰብዓዊነትን ታሳቢ በማድረግ ሊያስቆሙት ያሰቡት ተኩስ አቁም መሆኑንም አር ቲ ዘግቧል፡፡ የዩክሬን ኃይሎች በተኩስ አቁሙ መገዛት እንዳለባቸውም ሞስኮ ፍላጎቷ ሆኗል፡፡
የኪዬቭ ጦር ትንኮሳ ካደረገ ግን አጸፋዊ ምላሽ ክሬሚሊን ለመስጠት ይገደዳል ይላል አዋጁ፡፡ ፕሬዚዳንት ፑቲን በ2023 ለገና በዓል እንዲሁም በአሁኑ የፋሲካ በዓል ለ30 ሰዓታት ተኩስ አቁም አዋጅ ይፋ ማድረጋቸው አይዘነጋም ፡፡ ዘገባው የዋሽንግተን ፖስት እና አር ቲ ነው፡፡












