April 18, 2025
የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት ቀን በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ከተማ በደብረ ገነት መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን በፆም፣ በጸሎት እና በስግደት እየታሰበ ነው። የአዳም ልጆች 5 ሺህ 500 ዘመን ተፈርዶባቸው የነበረውን የሞት ፍርድ በሕይዎት ለመተካት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራኒዮ አደባባይ የሰው ልጅ ፍቅር ስቦት ስለ ዓለም አንድነት እና ስለ ሰላም ሲል የተሰቀለበት ዕለት መኾኑን የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብጹዕ አቡነ በርናባስ ተናግረዋል።

“የክርስቶስን ሕማማተ መስቀል የሚያስብ ሁሉ እርስ በርሱ ሊዋደድ ይገባል” ሲሉ የገለጹት ደግሞ የደብረ ገነት መድኃኒዓለም ደብር ዋና አሥተዳዳሪ እና የድጓ መምህሩ መልአከ ገነት ጸጋ ዘአብ ታደሰ ናቸው። ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ የተጣሉትን አስታርቋል፤ ያሉት የድጓ መምህሩ ይህንን የስቅለቱን ዕለትም የመስቀሉን በረከት ለማግኘት በፍጹም አንድነት እና በመተሳሰብ ሕመሙን እና ሞቱን ማሰብ ማክበር ይገባል ነው ያሉት። ዘገባው የአሚኮ ነው፡፡













