::::::::::::::::::::::::::::::::::
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከነገ ጀምሮ በአማራ ክልል የሚያካሂደውን የምክክር ሂደት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
ኮሚሽኑ ከ267 ወረዳዎች የተወጣጡ በአጠቃላይ ከ6 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ተወካዮች እንደሚሳተፉበት የተገለፀ ሲሆን፣ ለአንድ ሳምንት በሚቆየው ምክክር ሂደት አጀንዳቸውን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በምክክር ሂደቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ የአሠልጣኞች እና የተባባሪ አካላት ማሠልጠንን ጨምሮ ተወካይ የህብረተሠብ ክፍሎች በባህርዳር፣ ደሴ፣ ደብረ ብርሃን እና ጎንደር በተዘጋጁ በአራት ክላስተሮች ከ20 ሺህ በላይ ሠዎች በተሳታፊ ልየታ ተመርጠው አጀንዳዎቻቸውን እና የሚወክሏቸውን አካላት መምረጣቸው ተገልጿል፡፡
ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተሳታፊ መለየት እና በሁለተኛ ደረጃ እንደ ኢትዮጵያ መግባባት ያልተቻለባቸው ጉዳዮችን በአጀንዳነት በመስጠት የሚጠናቀቅ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ምክክሩ የህዝብ ድምፅ የሚደመጥበት እና በሠለጠነ ስርዓት ችግሩን የሚፈታበትን መንገድ ማመላከቻ መሆኑንም ተነስቷል፡፡
በክልሉ ያለው የሰላም ሁኔታ የምክክር ሂደቱን ሊረብሽ የሚችል ምንም አይነት ነገር እንደሌለ ማረጋገጥ መቻሉን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማሪያም ተናግረዋል።
በክልሉ በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙ ቡድኖች በግልፅ በምክክሩ ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ገልፀዋል።
በነገው እለት መጋቢት 27/2017 የሚጀመረው የአማራ ክልል የምክክር ሂደት ሚያዚያ 04/2017 ይጠናቀቀል።
ዘገባውን ከስፍራው ያደረሰን አክረም ኑርያ ነው::












