::::::::::::::::::::::::::::::::::::
የቱሪዝም ሚኒስቴር በቱሪዝም ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ላይ ነው።
በመድረኩ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ታድመዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትሯ ሰላማዊት ካሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ በርካታ ታሪካዊ፣ተፈጥሯዊ እና ሰውሰራሽ ሀብቶች ያሏት ሀገር ናት።
እንዲሁም በዘርፉ በቀዳሚ ተርታ የሚያስቀምጥ እምቅ ሀብት ያላት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
ከዘርፉ የሚገኘውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም ከጊዜው ጋር የሚራመድ የፖሊሲ ማእቀፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም የነበረው ፖሊሲ ረጅም ጊዜ ማስቆጠሩን እና በዘርፉ ያለውም እይታ በእጅጉ መቀየሩን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ዘርፉን ጊዜውን በዋጀመልኩ ለመምራት የሚያስችል የፖሊሲ ዝግጅት ሲካሄድ መቆየቱን ገልጸው፥ ባለፉት ጊዜያትም በርካታ አካላት የተሳተፉበት ውይይት በማድረግ ግብአት ሲሰባሰብ መቆየቱን አስታውሰዋል።
አዲሱ ፖሊሲ ዘርፉ የኢትዮጵያን ገጽታ በጉልህ ለመገንባት እንዲሁም ከዘርፉ የሚገኘውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ከመድረኩ የሚገኙ ግብአቶችን በዚሁ የፖሊሲ ዝግጅት ሂደት ውስጥ እንደሚካተቱ አመላክተዋል። ዘገባው የኢዜአ ነው፡፡












