የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) የቻውናውን ሻንሀይ ላውንች ዲዛይን አውቶሞቲቭ ኩባንያ ተወካዮችን በዛሬው ዕለት ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት አረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት መንግስት እየሰራ በመሆኑ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ማምረት ስራ መሰማራት እንደሚያዋጣው መከሩ።
ሻንሀይ ላውንች ዲዛይን አውቶሞቲፍ ኩባንያ የተለያዩ ዓይነት ተሽከርካሪዎችን በማምረት ለገበያ የሚያቀርብ እንደሆነ የኩባንያው ተወካዮች አብራርተዋል፡፡ ኩባንያው በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የአየር ታክሲና ሰው አልባ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ፣ አውቶሞቢሎችን፣ አውቶብሶችንና የጭነት ተሽከርካሪዎችን እንደሚያመርት ተናግረዋል። ስራ አስኪያጅ ው ሻውሀን ኩባንያው በኢትዮጵያ ውስጥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማምረት ላይ መሰማራት እንደሚፈልግ መግለፃቸውን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ኩባንያው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማምረት ስራ ቢሰማራ የበለጠ አዋጭ እንደሚሆንለትና ድጋፍ እንደሚደረግለት ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያና ቻይና ካላቸው ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አንፃር ኩባንያው በሚያደርገው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ከሚያገኘው ኢኮኖሚያዊ ትርፍ ባሻገር የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት የበለጠ ያጠናክራል ብለዋል፡፡ (ኤፍ ኤም ሲ)

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) የቻውናውን ሻንሀይ ላውንች ዲዛይን አውቶሞቲቭ ኩባንያ ስራ አስኪያጅ ው ሻውሀን












