።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
የአማራ ክልል አዲሱን የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ፈጥኖ በመተግበርና ውጤታማ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ገለጹ።
አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ የሚያስተዋወቅ መድረክ በባህር ዳር ከተማ ዛሬ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር)፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ ከተማ ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመዲን መሀመድ (ዶ/ር)ና ሌሎች የክልልና የፌደራል ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት፥ በክልሉ የግብርናው ዘርፍ ግንባር ቀደም የኢኮኖሚ አቅም በመሆኑ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ ነው።
ባለፉት 22 ዓመታት አገሪቱ ስትመራበት የነበረው የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ አሁን ላይ ካለው እድገትና የህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ መለወጥ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አንስተዋል።
ፖሊሲው ምርታማነትን በፊት ከነበረው በላቀ ደረጃ በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ መፍትሄ ሰጪ መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ መንግስትም የተሻሻለውን የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲውን ፈጥኖ በመተግበርና ውጤታማ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አሳስበዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ በክልሉ ያለው እምቅ የግብርናና የመልማት አቅም የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።
በዚህም ዘመናዊ አሰራርን ተጠቅሞ በማምረት በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ለማፋጠን የፖሊሲ ማሻሻያ መደረጉ ወቅቱን የጠበቀ ነው ብለዋል።
ፖሊሲውን ወደ መሬት በማውረድ እድገቱን ለማፋጠንና የህዝቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በየደረጃው ያለው አመራርና የዘርፉ ባለሙያ ሁሉን አቀፍ ጥረት ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
ዘገባው የኢዜአ ነው።












