፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ታህሳስ 24 2017| NBC ETHIOPIA- ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሩሲያ መንግስት እና የሀገሪቱ ትልቁ ባንክ የሆነው እስበር ባንክ (SBER.MM) ከቻይና ጋር በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ትብብር እንዲፈጥሩ አዘዙ።
የፑቲን መመሪያ ሩሲያ ከ ብሪክስ አጋሮች እና ከሌሎች ሀገራት ጋር በመተባበር አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን ለማዳበር እንደምትሰራ ካሳወቁ ከሶስት ሳምንታት በኋላ በክሬምሊን ድረ-ገጽ ላይ ወጥቷል።

ሞስኮ በዩክሬን ላይ የምታደርገውን ጦርነት ለማስቀጠል የምትፈልጋቸውን ቴክኖሎጂዎች እንዳትጠቀም ለመገደብ የታቀዱ የምዕራባውያን ማዕቀቦች የዓለም ዋና ዋና የማይክሮ ቺፕስ አምራቾች ወደ ሩሲያ የሚላኩ ምርቶችን እንዲያቆሙ አድርጓቸዋል፣ ይህም የ AI እድገቷን በእጅጉ ገድቦታል።

የእስበር ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጀርመን ግሬፍ እንደተናገሩት ሩስያ ከውጪ ይገቡ የነበሩ የAI ሞዴሎችን የሚደግፉ ማይክሮ ቺፖችን ወይም የግራፊክስ ማቀነባበሪያ ክፍሎችን (GPU) ለመተካት ባለመቻሏ ዘርፉን ለማሳደግ በእጅጉ ተቸግራለች።
ሩሲያ ምዕራባውያን ካልሆኑ አገሮች ጋር በመተባበር በ 21 ኛው ክፍለ ዘመን በጣም ተስፋ ሰጭ እና ወሳኝ ቴክኖሎጂዎች ውስጥ የአሜሪካን የበላይነት ለመገዳደር ትፈልጋለች።

ፑቲን ያለፈው ወር ውስጥ አዲስ የAI ትብብር ኔትወርክ እንደሚፈጥሩና ከብሪክስ እና ሌሎች ፍላጎት ካላቸው ሀገሮች ባለሙያዎችን በማሰባሰብ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ሩሲያ በአሁኑ ጊዜ በ AI ትግበራ ፣ ፈጠራ እና ኢንቨስትመንት ከ 83 አገሮች ውስጥ 31ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከቻይና ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የብሪክስ አባላት ህንድ እና ብራዚል ጭምር ወደኋላ ቀርታለች። ዘገባው የሮይተርስ ነው።
በ-ዳንኤል መኮንን












