፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨፨ ፨
አዲስ አበባ |ታህሳስ 24 2017| NBC ETHIOPIA- በአማራ ክልል የገናና የጥምቀት በዓላት በድምቀት እንዲከበር ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ለበዓላቱ አከባበር የተደረገውን ፖሊሳዊ ዝግጁነት አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር መሰረት ደባልቄ በመግለጫው እንዳሉት በዓላቱ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ለመሳብና ለገጽታ ግንባታ ያላቸው ፋይዳ የጎላ ነው።
በላሊበላ የገና እና በጎንደር የጥምቀት በዓላትን ለመታደም የሚመጡ ቱሪስቶች ቆይታቸው ሰላማዊና የተመቸ እንዲሆን ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በሁሉም የከልሉ አካባቢዎች በዓላቱ ያለምንም የጸጥታ ችግር አክብሮ ለማጠናቀቅ የሚያስችል ሥራ በየደረጃው መከናወኑን ረዳት ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
ለዚህም ኮሚሽኑ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከወጣቶችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት መደረጉን አመልክተዋል።
በተለይ በላሊበላና በጎንደር ከተሞች በበዓላቱ ወቅት ወንጀል ፈጽመው እጅ በእጅ ለሚያዙ ግለሰቦች አፋጣኝ ፍትህ ለመስጠት የሚችል የምርመራ ቡድን መደራጀቱንም ጠቁመዋል።
በበዓላት ገበያ ወቅት ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ህገ ወጥ ነጋዴዎችን ማህበረሰቡ ማጋለጥ እንዳለበት የገለጹት ሃላፊዋ፣ ማህበረሰቡ ለገበያ ሲንቀሳቀስ ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስበዋል።
በተጨማሪም በበዓል ወቅት ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር በስፋት ሊስተዋል ስለሚችል አርሶ አደሩ ተገቢ ጥንቃቄ እንዲያደርግም መልዕክት አስተላልፈዋል።ዘገባው የኢዜአ ነው፡፡












