፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ታህሳስ 14 2017| NBC ETHIOPIA- የናሽናል ሚዲያ አክሲዮን ማህበር(NBC ETHIOPIA) እና የኮሪያ ብሮድካስቲንግ ፋውንዴሽን (ኤራንግ) የይዘት ልውውጥ እና የሰው ሃብት ልማት ስምምነት ተፈራረሙ፡፡
በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ቾንግ ካንግ እና የናሽናል ሚዲያ አ.ማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ከበደ ስምምነቱን ዛሬ ታህሳስ 14 2017 ዓ. ም በኤን ቢሲ ኢትዮጵያ ስቱዲዮ ፈጽመዋል፡፡

በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ ኤምባሲ የስራ ሃላፊዎችና የናሽናል ሚዲያ አ.ማ (ኤን ቢ ሲ ኢትዮጵያ) አመራሮች በተገኙበት የተፈጸመው ስምምነቱ በኤን ቢሲ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተመረጡ የኮሪያ ድራማዎችንና ሪያሊቲ ሾዎችን (Reality shows) የማስተላለፍ መብት የተሰጠው ሲሆን የተመረጡ ሀገራዊ የኤን ቢሲ ኢትዮጵያ ፕሮግራሞች በተመሳሳያ በኮሪያ ማስተላለፍ የሚያስችል ነው፡፡

በስነ ስርዓቱ ላይ በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ቾንግ ካንግ የኤን ቢ ሲ ኢትዮጵያ አመራሮች እና ባለሙያዎች በኮሪያ ሚዲያዎች ልምድ እንዲያገኙ ፣ ከዛም አልፎ በስለጣናዎች እንደሚካፈሉ ገልጸዋል፡፡ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ባህልና ይዘት ተኮር ፕሮግራሞች የመጀመሪያ ትኩረታቸው አድርገው እንደነበር የገለጹት አምባሳደሩ ከናሽናል ሚዲና አክሲዮን አ.ማ ጋር ያደረጉት ስምምነት በር ከፋችና አብነትነት ያለው ነው ብለዋል፡፡

የናሽናል ሚዲያ አ.ማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ከበደ በበኩላቸው ኮሪያ በሚዲያና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ዓለም ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑት መሃል እየተሰለፈች መምጣቷን ገልጸው የይዘት ልውውጥ እና የሰው ሃብት ልማት ስምምነቱ የአፍሪካ የኢኮኖሚና የባህል ማዕከል ለመሆን እየሰራች ባለችው ኢትዮጵያ ለሚገኙ ሚዲያዎች ሰፊ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡
አክለውም ስምምነቱ የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ሁለንተናዊ ትብብርን ለማሳደግ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡












