፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ህዳር 11 2017| NBC ETHIOPIA- ከእስራኤል እንደሀገር መመስረት አንስቶ በጠላትነት ለዓመታት በአይነ ቁራኛ ሲተያዩ በቆዩት ታሪካዊ ጠላቶቹ ግብጽ እና እስራኤል መካከል ለሰላም ስምምነት መንገድ ጠርጓል የተባለለት ታሪካዊ ጉብኝት የተደረገው ከዛሬ 47 ዓመታት በፊት ልክ በዛሬዋ ዕለት በጎርጎሮሳውያኑ ሕዳር 20፣ 1977 ነበር፡፡ የወቅቱ የግብጽ ፕሬዝዳንት አንዋር ሳዳት የመጀመሪያው ብቻ ሳይሆን ብቸኛው የዓረቡ ዓለም መሪ በሚያደርጋቸው በእዚህ ጉዞ ሰላም እናውርድ ሲሉ ለእስራኤላውያን ጥሪ አቅርበውበታል፡፡
በጦርነት ወጪ የተራቆተው የሀገራቸው ምጣኔ ሃብት ላይ ነፍስ ለመዝራት ሀገሪቱ በጠላትነት ከምታያቸው ሀገራት ጋር እርቅ ማውረድ አለባት ያሉት ሳዳት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜናቸው ቢግን የተላከላቸውን የጉብኝት ጥያቄ መቀበላቸውን እንዳሳወቁ እስራኤል ለአቀባበል ሽር ጉድ ማለት ጀመረች፡፡ ጎዳናዎቿ በሁለቱ ሀገራት ባንዲራዎች ተጥለቀለቁ፤ “ሳዳት ወደእስራኤል እንኳን ደህና መጡ!” የሚሉ ጽሁፎች በየጎዳናው ተሰቀሉ፡፡
ሳዳት ለሁለት ቀናት ጉብኝት ወደጋባዧ ሀገር አቅንተው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢግን ጋር ተገናኙ፡፡ በማግስቱ በኢየሩሳሌም በሚገኘው አልአቅሳ መስጂድ ጸሎት ካደረሱ፤ የቅዱስ ሴፑልከር እና የያድ ቫሸም እልቂት መታሰቢያ ቤተ-ክርስቲያንን ከጎበኙ በኋላ በእስራኤል ፓርላማ ተገኝተው በአረብኛ አንድ ሰዓት የፈጀ ንግግር አደረጉ፡፡ ንግግራቸው ለግብጻውያን በቴሌቭዥን አማካኝነት እንዲተላለፍ ተደርጎ ነበር፡፡
የእስራኤልን ሀገርነት ተቀብያለሁ ያሉት ሳዳት በምላሹ በእስራኤል ቁጥጥር ስር ያሉ የሀገራቸው ግዛቶችን መልሱልን የሚል ማሳሰቢያ አዘል ጥያቄያቸውን አቅርበውበታል፡፡ ንግግራቸውን ሲጨርሱ 120 አባላት ያሉት የእስራኤል ፓርላማ ደማቅ ጭብጨባን ቸራቸው፡፡ ከፓርላማ መልስ ሳዳት እና ቢግን በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ቁርሾ ማብቃቱን እና በመካከለኛው ምስራቅ ሰላም ለማስፈን በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን እወቁልን አሉ፡፡ ከዓለም ዙሪያ የመጡ ጋዜጠኞች ይህንን ታላቅ ሁነት ለዓለም ህዝብ ለማድረስ ከወዲያ ወዲህ ተራወጡ፡፡

በእስራኤል የሞቀ አቀባበል የተቸረው የሳዳት ጉብኝት እና የእርቅ ዘመቻ በአብዛኞቹ የዓረብ ሀገራት ፍልስጤማውያንን እንደመክዳት ተቆጥሮ ቁጣን ጫረ፡፡ የሳዳትን ወደሀገር መመለስ ሳይጠብቁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እና ምክትላቸውን ጨምሮ በርካታ ባለስልጣናት ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ፤ ሶርያውያን በመዲናዋ ደማስቆ ከሰዓቱን እውቅና አንሰጥም በማለት የተቃውሞ ሰልፍ አደረጉ፤ መቀመጫቸውን በለንደን እና በተለያዩ የዓለም ሃገራት ያደረጉ የሊቢያ ዲፕሎማቶች የግብጽን ባንዲራ አቃጠሉ፤ የአረብ የሽምቅ ተዋጊዎች ሳዳትን ለመግደል ዛቱ፤ በዓረቡ ዓለም ውጥረት ነገሰ።
አሶሸትድ ፕረስ ስለጉዳዩ ሃሳባቸውን የጠየቃቸው ፍልስጤማውያን የሳዳት ድርጊት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል በሚል ትልቅ ስጋት ውስጥ እንደከተታቸው ሲገልፁ፤ እስራኤውያንም ለሳዳት እና ለሀገራቸው አስከፊ መዘዝን ያስከትላል ብለው ስጋታቸውን አጋርተው ነበር፡፡ የተፈራው አልቀረም፡፡ የሳዳት ድርጊት ግብፅን ከአረብ ሊግ አባልነት ውጪ አደረጋት፤ የባሰውንም ለሳዳት ሞት ምክኒያት ሆነ፡፡ ጥቅምት 1981 በመዲናዋ ካይሮ በተካሄደ ወታደራዊ ሰልፍ በስምምነቱ የተቆጡ የገዛ የሀገራቸው እስላማዊ ጂሃዲስቶች ገደሏቸው፡፡
የሳዳት ጉብኝት ከአንድ ዓመት በኋላ በካምፕ ዴቪድ ሀገራቸው ከእስራኤል ጋር ላደረገችው የሰላም ስምምነት፤ ብሎም በአረቡ ሀገራት እና በእስራኤል መካከል ከተደረገው አሰቃቂው የዮም ኪፑር ጦርነት ስድስት ዓመታት በኋላ በጎርጎሮሳውያኑ መጋቢት 26፣ 1979 በአሜሪካ በነጩ ቤተ-መንግስት ለተደረሰው የተሟላ የሰላም ስምምነት መሰረት ስለመጣሉ ይነገርለታል፡፡
ለግብጽ አሁናዊ ሁለንተናዊ አቋም በብዙ ለፍተዋል ለሚባሉት ሳዳት ሞት ምክንያት የሆነው እና ከሃዲ የሚል ስያሜ ያሰጣቸው ወደእስራኤል ያደረጉት ጉዞ ዛሬ ሁለቱ ሃገራት ዲፕሎማሲ፣ ኢኮኖሚ እና ደህንነትን ጨምሮ በበርካታ ዘርፎች በትብብር ለመስራታቸው ምክንያት ሆኗል።
ጥቅምት ሰባት ሐማስ በእስራኤል ላይ የሰነዘረውን ጥቃት መነሻ ያደረገውና ከጋዛ ጀምሮ አድማሱን ያሰፋው እስራኤል ከሄዝቦላህ እና አጋሮቹ ጋር የገባችበት ጦርነት እንደቀጠለ ሲሆን ግብጽ እስራኤል ለሃማስ በቀል ከምትሰነዝረው መጠነ ሰፊ ውድመትና የሰው ህይወት መጥፋት እያስከተለ ከሚገኘው ጥቃቷ እጇን እንድትሰበስብ እያሳሰበች ነው፡፡
በ-መቅደስ ደምስ












