፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ህዳር 04 2017| NBC ETHIOPIA- በካፒታል ገበያ እና በኢንቨስትመንቱ ዙሪያ የተሻለ አቅም ለመፍጠር ያለመ አለም አቀፍ ጉባኤ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው።
ጉባኤው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ከአፍሪካ ልማት ባንክ እና ከአለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (አይኤፍሲ) ጋር በቅንጅት ያዘጋጀው ነው።
”ቀጣይነት ያለው መንገድን ማበጀት” በሚል መሪ ቃል እየተከናወነ በሚገኘው ጉባኤ፤ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያን ማጠናከር እና አቅምን ማጠንከር ላይ ትኩረት ተሰጥቷል።
የገበያ ህጎችን መፈተሽ፣ የኢንቨስትመንት ዕድሎች ማስፋት፣ የፊንቴክ ፈጠራዎችን እና ዘላቂ ፋይናንስን ማጠርከር ጨምሮ በርካታ ከካፒታል ገበያ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችም የጉባኤው አጀንዳዎች ናቸው።
በመድረኩ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር)፥ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመነቃቃት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፥ በቅርቡ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ደግሞ ይህንን የሚደግፍ ነው ብለዋል።
እንደዚህ አይነት ጉባኤዎችም ልምድን ለመጋራትና ጤናማ የፋይናንስ ስርአት እንዲኖር የሚስችሉ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
የካፒታል ገበያው ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተህክሉ በበኩላቸው፥ በጉባኤው የሚነሱት ሀሳቦችና ልምዶች ለገበያው ጥንካሬና ቁጥጥር ግብአት ሆኖ እንደሚያገለግል ገልጸዋል።
የብሄራዊ ባንክ ገዢው ማሞ ምህረቱ ጉባኤው ከጫፍ የደረሰውን የካፒታል ገበያው በቁጥጥር ረገድ እንዲጠነክር የሚያደርግ ይሆናል ብለዋል።
ጉባኤው ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን የኢትዩጵያ መዋለ ነዋይን ለህዝብ ሽያጭ ማቅረብና የግብዓት መመሪያ ይፋ ይሆንበታል ተብሏል።
በ-ሰላማዊት ወንድወሰን
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook- https://web.facebook.com/ethiopiannbc/
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












