፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | መስከረም 23 2017| NBC ETHIOPIA-ኢሬቻ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ የህዝቦችን አንድነትና አብሮነት በጠበቀ መልኩ እንዲከበር በርካታ የዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገልጿል።
የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ጀሚላ ሲምቢሩ በዓሉን ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ የተከናወኑ የዝግጅት ሥራዎችን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ኢሬቻ የገዳ ሥርዓት መገለጫ የአንድነት፣ አብሮነትና የሰላም በዓል ነው ብለዋል።
የበዓሉ ታዳሚዎች ያለ ኃይማኖትና ፖለቲካ ልዩነት ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ብቻ በዓሉን በጋራ እንዲያከብሩም ጥሪ አቅርበዋል።
በዓሉ ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበርም ከበርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተደረገ ውይይት መግባባት ላይ መደረሱንም ነው የገለፁት።
በበዓሉ ላይ አባ ገዳዎች ባስተላለፉት መሠረት የሕዝቦችን አንድነት፣አብሮነትና ወንድማማችነት የሚያንጸባርቁ መልዕክቶች ብቻ መተላለፍ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በጋር በመሆን የሆራ ፊንፊኔን የማጽዳትና ለሥርዓቱ ምቹ የማድረግ ሥራ መሠራቱንም ጠቁመዋል።
የክልሉ መንግሥት ባስተላለፈው መልዕክት መሠረትም በዓሉ ላይ ለመታደም ከውጪ አገራት ለመጡ እንግዶችም አቀባበል መደረጉን አስረድተዋል።
በመገናኛ ብዙኃን በዓሉን አስመልክቶ የሚተላለፉ መልዕክቶች አንድነትን፣ ኅብረትን፣ አብሮነትንና ወንድማማችነትን የሚያንጸባርቁ እንዲሆኑም ከባለሙያዎች ጋር ውይይት መካሄዱንም ጠቁመዋል።
በዓሉ ላይ የሚታደሙ እንግዶች ድንገተኛ የጤና እክል የሚያጋጥሙ ከሆነም አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል።
በዚህም ሕዝባዊ በዓል ላይ ከአባ ገዳ ሰንደቅ ዓላማ ውጪ ሌሎችን ይዞ መገኘት የተከለከለ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በዓሉ ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ ብሎም የሕዝቦችን አንድነት፣አብሮነትና ወንድማማችነት በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook – https://www.facebook.com/ethiopiannbc/
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












