፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | መስከረም 23 2017| NBC ETHIOPIA- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከቆቃ-ሁርሶ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ጥምር የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ በተፈፀመ ስርቆት ኃይል መቋረጡን አሰታወቀ።
የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ በምስራቅ የሃገሪቱ ክፍል ለሚገኙ ከተሞችና አካባቢዎች፣ ለአዲስ አበባ- ጅቡቲ የባቡር መስመር እንዲሁም ለጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበ እንደነበረ ተጠቁሟል።
በአፋር ክልል አዋሽ ፈንታሌ ወረዳ በንቲ ቀበሌ ልዩ ስሙ አዋሽ ፓርክ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ የኃይል ተሸካሚ ምሰሶ ላይ በተፈፀመ ስርቆት በተጠቀሱት ቦታዎች የኃይል አቅርቦት መቋረጡን ጠቅሰዋል።
ከወደቀው አንድ ምሰሶ በተጨማሪ ሰባት የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች በአስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ተብሏል።

በማዕከላዊ ሁለት ሪጅን የኃይል ማስተላለፊያዎችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ዘበርጋ እንደገለፁት፣ ጉዳት የደረሰበትን የኃይል ተሸካሚ ምሰሶ ለመቀየር የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን ተዋቅሮ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።
ጥገናውን ለማከናወን ተመሳሳይ የመለዋወጫ ዕቃዎችን የመለየትና የማጓጓዝ ሥራዎች እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ስርቆት የተፈፀመበት የኃይል ተሸካሚ ምሰሶ ጥምር የኤሌክትሪክ መስመሮችን የያዘ በመሆኑ የጥገና ሥራው ከ20 ቀን ያላነሰ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ገልፀዋል።
በሌላ በኩል ከመተሃራ – አዋሽ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የባቡር መስመር ላይ በሚገኙ ዘጠኝ የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ ጉዳት በመድረሱ የጥገና ሥራዎችን ለማከናወን ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም ተገልጿል።
በአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ በኃይል ማስተላለፊያ ተሸካሚ ምሰሶ አካላት ላይ እየተፈፀሙ የሚገኙ የስርቆት ወንጀሎች መበራከታቸውን የገለፁት አቶ አለማየሁ ለኃይል መሰረተ ልማቶች ተገቢው ትኩረት እንዲሰጡ ማቅረባቸውን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook – https://www.facebook.com/ethiopiannbc/
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












