፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | መስከረም 09 2017| NBC ETHIOPIA- ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና መርህን መሰረት ያደረገ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማራመድ እንደምትፈልግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በኢትዮጵያ ወቅታዊ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ላይ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
አምባሳደር ነብያት በመግለጫቸው፣ ኢትዮጵያ ቀጣናውን የትርምስ አውድማ ለማድረግ የሚደረገው እንቅስቃሴ ሊቆም ይገባል የሚል ጽኑ እምነት እንዳላት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቅድሚያ ለጎረቤት ሀገራት መሆኑን ገልጸው፣ የጎረቤት ሀገራት ሰላም የተሳለጠ እንዲሆን ኢትዮጵያ አበክራ ትሰራለችም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላምና በመሰረተ ልማት የተሳሰረ ጉርብትና እንዲኖር ንቁ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ማንም ለሚያነሳው ሀሳብ ምላሽና እንካስላንትያ እንደማትገጥም ገልጸው፣ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን የትርምስ አውድማ ለማድረግ የሚስተዋለው እንቅስቃሴ ግን ሊቆም ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መርህ ችግሮችን በሰከነ ውይይት መፈታት አለበት የሚል ነው ያሉት አምባሳደር ነብያት፣ ነገር ግን ጉዳዩን መስመር እንዲስት ለማድረግ የሚሰነዘሩ ሀሳቦች ተገቢ አይደሉም ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከመስከረም 14 እስከ 20 ቀን 2017 በመሪዎች ደረጃ በሚከናወነው 79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በንቃት ለመሳተፍ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በተመድ ጠቅላላ ጎባኤ ለ79 ዓመታት በንቃት መሳተፏን የገለጹት አምባሳደር ነብያት፣ በቀጣዩ ጉባኤም የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካን ጥቅም በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ በንቃት ትሳተፋለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከዋናው ጉባኤ ጎን ለጎን በብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ በንቃት ትሳተፋለች ብለዋል።
በተጨማሪም ከአትሚስ (የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ) ሰራዊት አዋጭ ሀገራት ጋር የጎንዮሽ ውይይት እንደምታደርግም ገልጸዋል።
ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩ ሁለንተናዊ ግንኙነቶች ላይ ለመወያየት ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook – https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












