፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | መስከረም 08 2017| NBC ETHIOPIA-በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮ-ፈረንሳይ የወዳጅነት ቡድን በፈረንሳይ ፓርላማ የአፍሪካ ቀንድ የወዳጅነት ቡድን ፕሬዝዳንት ሴናተር ሁግ ሳሪ የተመራው ልዑክ ጋር ተወያየ።
በኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮ-ፈረንሳይ የወዳጅነት ቡድን ዋና ሰብሳቢ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ ለረጅም አመታት የቀጠለው የኢትዮጵያና የፈረንሳይ ወዳጅነት የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ብሄራዊ ጥቅምን መሠረት ያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የዜጎችን ሁለንተናዊ አቅም የሚያጎለብቱ የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን በመስራት ላይ እንደምትገኝና ሪፎርሙ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ወዳጅ ሀገራት ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
በአፍሪካ ቀንድና በመላው አለም የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ አሸባሪዎችን ከመዋጋት አኳያ ኢትዮጵያ ከፈረንሳይና ከሌሎች አጋር ሀገራት ጎን እንደምትቆምም ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመተባበርና የጋራ ጥቅምን መሰረት ያደረገ ግንኙነት በመፍጠር አካባቢያዊ ሰላም እንዲረጋገጥ ጠንክራ እየሰራች ነው ሲሉም አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡
ሴናተር ሁግ ሳሪ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለፈረንሳይ ታሪካዊ አጋር ሀገር መሆኗን የገለጹ ሲሆን፤ በአፍሪካ ቀንድ እና በመላው አፍሪካ ሽብርተኞችን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ፈረንሳይ ከኢትዮጵያ ጋር ተባብራ እንደምትሰራ ገልጸዋል፡፡
የዜጎችን ሰላምና ደህንነት እንዲሁም የሀገርን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እንዲሁም አስተዳደራዊ ዕድገትን በዘላቂነት ለማስቀጠል በየትኛውም ቦታና ሁኔታ ሰላምና መረጋጋት ያስፈልጋል ያሉት ሴናተሩ፤ ለዚህም በአፍሪካ ቀንድ እና በመላው አፍሪካ ፈረንሳይ ከአጋሮቿ ጋር በትብብር እና የጋራ ብሔራዊ ጥቅምን መሰረት ባደረገ መልኩ እንደምትሰራም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የጀመረቻቸውን የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን ከመደገፍ አኳያም ፈረንሳይ ትብብር ታደርጋለች ብለዋል፡፡ በፓርላማ ዲፕሎማሲ፣ በሕዝብ-ለሕዝብ ዲፕሎማሲ፣ በምርጫ ስርዓትና አፈጻጸም፣ በምክር ቤቱ ስልጣንና ተግባራት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ላይ ያተኮሩ ውይይት ማድረጋቸውን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመለክታል።
📌YouTube – https://www.youtube.com/@NBCETHIOPIA
📌 TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
📌Website – https://nbcethiopia.com/news/
📌Facebook – https://www.facebook.com/ethiopiannbc
#NBC_ETHIOPIA
#ሆኖ_መገኘት












