፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ጳጉሜ 2 2016| NBC ETHIOPIA- ባለፉት የለውጥ ዓመታት ተግባራዊ የተደረጉ የሪፎርም ስራዎች ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚ መገንባት ያስቻሉ ናቸው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ተናገሩ።
ጳግሜን 2 የሪፎርም ቀን “ሪፎርም ለላቀ አገልግሎት” በሚል መሪ ሃሳብ በሳይንስ ሙዚየም የፓናል ወይይት እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ ላይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፣ ሚኒስትሮችና አምባሳደሮች ተገኝተዋል።

ባለፉት ስድስት የለውጥ ዓመታት በኢኮኖሚ፣ በፍትህ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በትምህርት እንዲሁም በሲቪል ሰርቪስ ዘርፍ የተገኙ ስኬቶችና ቀጣይነት ያላቸው ስራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ በየዘርፉ ተግባራዊ የተደረጉ የለውጥ ስራዎች ችግሮችን ተቋቁሞ ዘላቂ ዕድገትን ማረጋገጥ ያስቻለ ውጤት የተገኘበት ነው።
በኢኮኖሚው መስክ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የኑሮ ውድነትን ችግር መቀነስ፣ የወጭ ንግድ ሚዛንን ማስተካከል ላይ የተወሰዱ እርምጃዎች ውጤት ያመጡ ናቸው።
ተግባራዊ የተደረጉ የገንዘብ ፖሊሲዎች፣ የብድርና የዕዳ ጫናን ለመቀነስ የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ ሆነዋል፤ የታክስ ፖሊሲውም የመንግስት ገቢ እንዲጨምር አድርጓል ብለዋል። ተግባራዊ በተደረጉ የለውጥ ስራዎች በየዓመቱ በአማካኝ 7 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሰዋል።

ከትምህርት ጋር በተያያዘ ከ30 ሺህ በላይ የአጸደ ህጻናት ትምህርት ቤቶችን ከመገንባት ባሻገር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል።
ከትምህርት ጥራት ጋር በተገናኘም አዳዲስ አሰራሮችን መዘርጋት፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ስራዎችም እንዲሁ ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።

እንደ አቶ አደም ገለጻ በፍትህ ዘርፉ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መርህን የተከተሉ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ስራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት።
ፍርድ ቤቶችም ነጻና ገለልተኛ መሆናቸው ከለውጡ ትሩፋቶች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሪፎርሙ የለውጡ ውጤቶችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው በዚህ ላይ ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ነው ያሉት።












