፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
የተወለዱት ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች ነው የክረምቱን ወራት በእርሻ እና በአደን እንደሚያሳልፉ ይናገራሉ ፡፡ ለበርካታ ዓመታት በግብርና እና በፋብሪካ ሥራ ላይ ተሰማርተውም ይሰሩ ነበር ፡፡
ከመምህርነት እስከ እግር ኳስ አሰልጣኝነት ከውትድርና እስከ የሚኒሶታ ግዛት ገዥ እስከመሆን ደርሰዋል ፡፡ 41ኛው የግዛቷ አስተዳዳሪ እንደማለት ነው ህዳር ላይ በሚደረገው የአሜሪካ 2024ቱ ምርጫ ተወዳዳሪዋ ካማላ ሀሪስ የሚያሸንፉ ከሆነ ምክትሌ ይሆናሉ ብለው የመረጧቸው ቲም ዎልዝ ፡፡
እ.ኤ.አ በ1964 በኔብራስካ ገጠራማ ክፍል የተወለዱት ቲም ዋልዝ የሀይስኩል ትምርታቸውን እንዳጠናቀቁ በ17 አመታቸው የሀገሪቱን መከላከያ ብሄራዊ ጥበቃ በመቀላቀል በጦሩ ውስጥ ለ24 አመታት ማገልገላቸውን ታሪካቸው ያወሳል ፡፡
በተጨማሪም ለበርካታ ዓመታት በግብርና እና በፋብሪካ ሥራ ላይ ተሰማርተው ይሰሩ እንደነበር ይነገራል፡፡ከውትድርና ህይወት እራሳቸውን ማግለላቸውን ተከትሎ በመምህርነት በአሜሪካ ሳውዝ ዳኮታ ፣ ሚኒሶታ እንዲሁም በቻይና በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ሲያስተምሩ ቆይታዋል ፡፡

ዋልዝ በ1989 ከቻድሮን ስቴት ኮሌጅ በማህበራዊ ሳይንስ ዲግሪ እና በ2001 ከሚኒሶታ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በትምህርት አመራር educational leadership ማግኘታቸውን የትምህርት መረጃቸው ያመላክታል ፡፡
ቲም ዋልዝ ወደ ፖለቲካው አለም ብቅ ያሉት በ2004 በማሳቹስቴት ግዛት የሴናተር ጆን ኬሪ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ውስጥ በበጎ ፍቃደኝነት ከተቀላቀሉ በኋላ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
በወቅቱ የሀይስኩል አስተማሪ ስለነበሩ ተማሪዎቻቸውን በ George W. Bush የምርጫ ስብሰባ ላይ ለማሳተፍ ይዘው ሲሄዱ የጸጥታ አካላት በአንድ ተማሪ ቦርሳ ውስጥ ጆን ኬሪን ምስል በማግኘታቸው ተማሪውን ፖለቲካ ነክ ጥያቄዎች ሲጠይቁ በማየታቸው ተናደው ወደ ጆን ኬሪ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ ቡድን መቀላቀላቸውን ተናግረዋል ፡፡
ከሁለት አመት በኃላም ለመጀመሪያ ጊዜ ለአሜሪካ የኮንግረንስ ምክር ቤት አባልነት በመወዳደር አሸናፊ መሆን ችለዋል፡፡ በ2008ትም በሚወዳደሩበት አካባቢ 62 በመቶ ድምጽ በማግኘት ዳግም አሸንፈው ሁለተኛ ዙር ምርጫን ከሪፐብሊካኖች ውጪ በሙሉ ድምጽ ያሸነፈ ሁለተኛው ሰው መሆን ችለዋል ፡፡
ዋልዝ የደቡባዊ ሚኒሶታ የገጠራማውን ክፍልን በመወከል በምክር ቤት አባልነታቸው ለአምስት ተከታታይ ጊዜያት በተደጋጋሚ በማሸነፍ በኮንግረሱ በተለያዩ የስራ ሃላፊነት ሲሰሩ ቆይተዋል ፡፡
በ2018ቱ የሚኒሶታ ግዛት አስተዳዳሪነት ምርጫ የሪፐብሊካኑን ተወካይ ተፎካካሪያቸውን በመርታት አሸንፈዋል፡፡
ይህንንም ተከትሎ በሪፐብሊካኖች ተይዞ የቆየውን የሚኒሶታ ፖለቲካዊ የበላይነት ከ2014 በኃላ ለመጀመሪ ጊዜ በዲሞክራቶች ቁጥጥር ሥር ማድረግ ችለዋል ፡፡
በ2022 በተደረገ ምርጫ ዳግም አሸንፈው በሚኒሶታ አስተዳደሪነታቸው ላይ ይገኛሉ ፡፡

የኮቪድ ወረርሽኝ እና እሳቸው በሚያስተዳድሩት ግዛት ጆርጅ ፍሎይድ የተባለ አንድ ጥቁር አሜሪካዊ በነጭ ፖሊስ በአሰቃቂ መንገድ በመግደሉ ከግዛቷ አልፎ በመላው አለም በርካታ ተቃውሞ ያስተናገደ ነበር ፡፡ በዚም በርካታ ሪፐብሊካኖች ትችቶችን ሲሰነዝሩባቸው ቆይተዋል ፡፡
ይህም የስልጣን ዘመናቸው ላይ ጥላ አጥልቷባቸው እንዳለፈ ቢቢሲ በዘገባው አስነብበቧል ፡፡ በሁለተኛው በግዛት አስተዳዳሪነት ዘመናቸው የኮሌጅ የትምህርት ወጪን መሸፈን ለማይችሉ ተማሪዎች ድጋፍ እንዲደረግ ፣ በሚኒሶታ የመንግስት ትምህርት ቤቶች የቁርስ እና የምሳ ምገባ በነጻ እንዲጀመር ፣ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው ስደተኞች የመንጃ ፈቃድ እንዲያገኙ እንዲሁም የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ህግን አውጥተዋል ፡፡በአሁኑ ጊዜም የዴሞክራት አስተዳዳሪዎች ህብረት ሊቀመንበር ናቸው::
በመከላከያው እና በሲቭል አገልግሎት በነበራቸው አበርክቶ በዜጎች ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፉ ሰው መሆናቸው ይነገርላቸዋል ፡፡ የዴሞክራት እና ሪፐብሊካኖች በእኩል ቁጥር በሚገኙባት ሜኔሶታ ያለቅሬታ ማስተዳደር መቻላቸው ደግሞ ጥሩ የፖለቲካ ልምድ እንዲያካብቱ እንዳገዘቸው በርካቶች ይመሰክሩላቸዋልል ፡፡
ለምክትል ፕሬዝዳንትነት ከቀረቡ ሰባት እጩዎች መካከል ካማላ ሀሪስ እሳቸውን መምረጣቸው ይህንኑ ከግንዛቤ በማስገባት እንደሆነም ተነግሯል ፡፡
የአሜሪካ ምርጫ በሚቀጥለው ጥቅምት ሲደረግ ካማላ ሃሪስ ቲም ዋልዝን ፤ዶናልድ ትራምፕ ጄዲ ቫንስን ምክትላቸው አድርገው ይፎካከራሉ፡፡












