፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሐምሌ 04 2016| NBC ETHIOPIA-እጅግ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች በመገኘቱ ገና በአፍላ እድሜው ወደ ስራ እንዲገባ እና ከሀገር ሀገር እተዘዋወረ ኑሮን እንዲለማመድ ተገዶ ነበር፤ አሁን ያለበትን የትወና ስራ ለማግኘት እና አሁናዊ ደረጃው ላይ ለመድረስም ያለፈበት ሂደት ቀላል የሚባል አይደለም ተወዳጁ እና ታዋቂው የአሜሪካን አክተር ቶማስ ክሩስ ማፓዘር ወይንም ቶም ክሩስ
የአይሪሽ፤ እንግሊዝ እና ጀርመን የዘር ሀረግ ካላቸው ቤተሰቦቹ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1962 በወረሃ ሀምሌ ሴራኪዩስ ኒውዮርክ ውስጥ ነው ይህቺን ምድር የተቀላቀለው፡፡
ከልዩ ፍላጎት መምህር እናቱ እና ኤሌክትሪካል ኢንጂነር ከነበረው አባቱ የተወለደው ቶም ክሩስ፤ ጥሩ በማይባል የቤተሰብ ሁኔታ ውስጥ ማደጉን የህይወት ታሪኩ ይናገራል፡፡ በቤተሰቡ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ምክንያት ከሀገር ሀገር ከከተማ ከተማ በመዘዋወር የልጅነት ወቅቱን አሳልፏል፡፡
በ8 አመቱ ጋዜጣ ማዞር፤ ፖስት ካርድ መሸጥ፤ጽዳት እና ሌሎች ስራዎች ውስጥ በመግባት የቤተሰቡን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ይጥርም ነበር፡፡በ14 አመታት የትምህርት ቆይታው ከ15 ትምህርት ቤቶች በላይ በመዘዋወርም ከስራ ባሻገር የቀለም ትምህርቱን ይከታተል ነበር፡፡

ፈጣን አይምሮ የነበረው ቶም በትምህርት ቤት ቆይታው ለሳይንስ ካለው ፍቅር ባሻገር ለአሁን እንጀራው መሰረት የሆነለትን የትወና ስራ በትምህርት ቤት የድራማ ክበብ ውስጥ በመሳተፍ ማደበር ችሏል፡፡
በፈረንጆቹ 1978 ገደማ ወላጅ እናቱ ይኖሩበት ከነበረው ካናዳ ባለቤቷን በመፍታት ሌላ ባል አግብታ ወደ አሜሪካ ኒው ዮርክ ትመለሳለች፤ ቶም ክሩስም በካቶሊክ ትምህርት ቤት በመግባት ትምህርቱን እንዲከታተል ይሆናል፤ ነገር ግን ለትወና ካለው የበዛ ፍቅር እና በሚያደርጋቸው አንዳንድ ሁነቶች ከሚማርበት የካቶሊክ ትምህርት ቤት እንዲሰናበት ይሆናል፡፡
በአንድ ወቅት በሰጠው ቃለ መጠይቅ የካቶሊክ ቄስ የመሆን እና የሀይማኖታዊ ትምህርቶችን የመማር ፍላጎትም እንደነበረው፤ ነገር ግን ከካቶሊክ ትምህርት ቤቱ ህልሙን ሳያሳካ መሰናበቱን ተናግሯል…በህይወቴ በርካታ ሁነቶችን መሞከር ያስደስተኛል በአንድ ወቅት የትምህርት ቤት የእግር ኳስ ክለብ ውስጥ እሳተፍም ነበር ነገር ግን አልኮል ስጠጣ ተገኝቼ ተባረርኩ በማለት በሁነቶች ላይ ረዥም ጊዜ ማሳለፍ እንደሚቸግረው ተናግሯል፡፡
የሀይስኩል ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ በሚኖርበረት ኒውዮርክ ከተማ የህይወት ጥሪዬ ብሎ ያሰበውን የትወና ስራ ማሰሱን ተያያዘው፤ ቀስ በቀስ በፊልሞች ላይ ትንንሽ ገጸባህሪትን በመስራት መንገዱን ጀመረው፡፡
ወደ እውቅናው አለም ለመምጣጥ እና ዋና ገጸ ባህሪ ተላብሶ ለመስራት በርካታ ጊዜያት እንደፈጀበት፣በኢንደስተሪው ለመቆየት ፈተናዎችን በጽናት በማለፍ ዛሬን ተመልክቷል፡፡
አንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ 1980ዎቹ መጀመሪውን ኢንድ ለስ ላቭ የተሰኘ ፊልም ላይ መሳተፍም ችሏል፡፡ይህ አጋጣሚ ሰፊውን በር የከፈተለት ቶም ክሩስ ከ72 የበለጡ ፊልሞች ላይ መሳፍ ችሏል፡፡ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ በማለፍ ዛሬ ላይ የደረሰው ቶም ክሩስ በሆሊውድ መንደር ካሉ የምንግዜም ተወዳጅ እና ምርጥ ተዋንያን መካከል ግንባር ቀደሙ መሆን ችሏል፡፡ቶም ከሩስ ለትወና ሞያ ካለው የላቀ ፍቅር እንዲሁም

በአካል ብቃት የጎለበተ በመሆኑ የሚሰራቸውን እያንዳንዱን አክሽን ፊልሞች እና ለአደጋ የሚያጋርጥ ሲኖችን ሳይቀር ያለ ስታን ማን እንደሚተውናቸው ተናግሯል፤ በዚህም በበርካታ ጊዜያት ቀላል የማይባሉ ጉዳቶችን አስተናግዷል፡፡
ብዙዎች ስለትወና ብቃቱ ደጋግመው የሚናገሩለት ቶም ከሰራቸውም የምንጊዜም ተወዳጅ ስራዎች መካከል risky business; mission impossible 1 and 2; war of the world፤ the color of money፤ ቶፕ ገን እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡
በሆሊውድ መንደር ካሉ ተዋንያን በመልካም ስብዕናው፤ በመልከ መልካምነቱ፤ በትወና ችሎታው፤ ባለው ስኬት እና ሌሎችም የእርሱ ምልክቶች ሆነው ዘልቀዋል፡፡People’s choice፤ golden globe፤ mtv movie award በተደጋጋሚ በምርጥ ተዋናይነት ዘርፍ ከወሰዳቸው ሽልማቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
በስራው እና በግል ህይወቱ ስኬታማ ጊዜያትን ያሳለፈው ቶም ክሩስ የ 3 ልጆችም አባት ነው፤62ኛ አመቱ ላይ የሚገኘው ቶም ክሩስ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ቢታለፍም ጠንክሮ በመስራት እና በጽናት ሁነቶች እንደሚለወጡ ምሳሌ መሆን የቻለም ነው፡፡ቶም ክሩስ በሆሊውድ ከፍተኛ ክፍያ ከሚከፈላቸው ተዋንያን መካከል አንደኛው ነው፤ያ በ8 አመቱ ቤተሰቡን ለመደገፍ ይፍጨረጨር የነበረው ጨቅላ አሁን ላይ ከ500 ሚሊዮን ዶላር የሚልቅ የሀብት መጠን አካብቷል፡፡
በ-የአብስራ ብርሀኑ












