፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሐምሌ 01 2016| NBC ETHIOPIA-ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ “ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ ማጠናቀቅን ባህል ያደረገችው አዲስ አበባ ዛሬም ተጨማሪ ብስራት ለነዋሪዎቿ እነሆ ብላለች ” ብለዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ከአራት ኪሎ ፣ ቀበና እስከ ኬኒያ ኤምባሲ ያለው መንገድ በኮሪደር ልማት ስራ አልምቶ እና አስውቦ ለነዋሪዎች አገልግሎት እንዲውል ክፍት ማድረጉን የገለጹት ከንቲባዋ ይህም ሶስተኛው የተጠነቀቀ የኮሪደር ስራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ አዲስ አበባን እንደስሟ ውብ አበባ እና ለመኖር ምቹ የሆነች ከተማ በማድረግ ዓለም-አቀፍ የስበት ማዕከልና የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የገባውን ቃል በተግባር እያሳየ መሆኑንም ከንቲባዋ አንስተዋል፡፡
በዚህም ምቹ የእግረኛ መንገዶችን ፣ የሞተር አልባ(ብስክሌት) መንገዶች ፣ ምቹ የታክሲ/ባስ ማውረጃና መጫኛ ስፍራዎችን ፣ የመኪና ፓርኪንጎችን ፣ አረንጏዴ ስፍራዎችን ፣ የመንገድ ዳርቻ ማረፊያ መቀመጫዎችን ፣ የህዝብ መናፈሻዎችን ፣ የከተማዋን ስታንዳርድ የሚመጥኑ መብራቶችንና ፉዋፉዋቴዎችን ባጠረ ጊዜ ገንብቶ አዲስ አበባ ከተማን 24 ሰዓት የደራችና ከቆሻሻ በእጅጉ እየጸዳች ያለች ከተማ መደረጉን ገልጸዋል::

የኮሪደር ልማት ስራ የተሰራባቸው አካባቢዎች የተሳለጠ ትራንስፖርትና ምቹ የመኖሪያ አካባቢን ከመፍጠር በተጨማሪ ለበርካቶች የስራ እድል የፈጠሩ እና 24/7 በመስራት አዲስ የስራ ባህል ያስተዋወቁ መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
“ለህዝባችን በገባነው ቃል መሰረት አዲስ አበባን አለምአቀፍ ተወዳዳሪ የሆነች ዘመናዊ ከተማ የማድረግ ስራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” ሲሉም ገልጸዋል::
ይህ ኮሪደር እውን እንዲሆን ፕሮጀክቶቹን በመከታተል የደገፉ፣ በትጋት ያስተባበበሩ፣ ከሁሉ በላይ በእልህ አስጨራሽ ሁኔታዎች ሁሉ ውስጥ በትዕግስት ከከተማ አስተዳደሩ ጎን በመቆም የደገፉ አካላትን ከንቲባዋ አመስግነዋል፡፡

“በተለይም መሬታችሁን ለልማት የለቀቃችሁ ፣ ከመኖሪያ አካባቢያችሁ ያዘዋወርናችሁ የከተማችን ነዋሪዎች በቀና ትብብራችሁ እና ከራስ በላይ ለትውልድ ዘላቂ ልማት በማሰብ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድናሳካው አቅም ስለሆናችሁን እጅግ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ፤አዲስ አበባ ታመሰግናችኃለች” ሲሉም ምስጋናቸውን አቅርበዋል::
YouTube – https://www.youtube.com/@NBCEthiopiaSC
TikTok – https://www.tiktok.com/@nbcethiopia
Facebook – https://www.facebook.com/ethiopiannbc
Telegram-https://t.me/nbcethiopiatv












