፨ ፨ ፨ ፨ ፨ ፨
አዲስ አበባ | ሰኔ 28 2016| NBC ETHIOPIA-በአለም ላይ ለማመን የሚያዳግቱ ነገር ግን እውን የሆኑ በርካታ ክስተቶች አሊያም እውነታዎች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ እውነታዎች እምብዛም የተለመዱ አለመሆናቸው ለብዙዎች ግርምትን የጫሩ ናቸው ፤በታሪክም አይረሴ የሆኑ ጭምር፡፡ ለዛሬ አስገራሚ ናቸው ብለን የመረጥናቸውን አምስት እውነታዎችን እነሆ፡፡
በበረሃማ ስፍራዎች ዝናብ ብርቅ ነገር ነው፤እንዳጋጣሚ ከጣለም ዝቅተኛ የዝናብ መጠን እንደሆነ ይታወቃል። በሰሃራ በረሃ የጣለው ዝናብ ግን በረዶን የቀላቀለ ጭምር ነበር ሲባል ለማመን የሚያዳግት ይመስላል፡፡ይበልጥ አስገራሚም ይሆናል፡፡
በፈረንጆቹ 2018 ነበር የአለማችን ሞቃት በሆነው ስፍራ ሰሃራ በረሃ ላይ ይህ ተከስቷል፡፡ የሰሃራ በረሃ በ2018 በጣለው ከባድ ዝናብ ስፍራው ሙሉ በሙሉ በነጭ በረዶ ተሸፍኖ የነበረ ቢሆንም በረዶው በበረሃው ላይ ሳይቀልጥ መቆየት የቻለው ግን ለአንድ ሰዓት ብቻ ነበር፡፡

በበረሃ ላይ የሚጥል የበረዶ ዝናብ መጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበው በ1979 ነበር፡፡ የበረዶ ግግሩ ለግማሽ ሰዓት ያህል ብቻ ነበር የቆየው፡፡ በ2018 በረዶ የቀላቀለ ዝናብ የጣለበት የሰሃራ በረሃ ከ6,000 ዓመታት በፊት ጥቅጥቅ ባሉ እፅዋቶች የተሞላና ከፍተኛ ዝናብ ያለው ለምለም ደን እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ፡፡ አሁን ላይ የአለማችን ሞቃታማ በረሃ በመሆኑ ይታወቃል።
ኮካ ኮላ በአለም ላይ በየትኛውም ቦታ ሊገኝ የሚችል ምርት እንደሆነ በርካቶች ያስባሉ፡፡ ነገር ግን በእነዚህ ሁለት ሀገራት የኮካ ኮላ ምርትን ማግኘት በፍጹም አይችሉም፡፡እነዚህም ሀገራት ሰሜን ኮሪያና ኩባ ናቸው፡፡

ሰሜን ኮሪያ ከ1950 ኩባ ደግሞ ከ1962 ጀምሮ ኮካ ኮላ ወደ ሀገራቸው እንዳይገባ ተደርጓል፡፡የዚህም መንስኤ አሜሪካ ስትሆን ሁለቱ ሀገራት በረጅም ጊዜ የአሜሪካ የንግድ እገዳዎች ውስጥ መሆናቸውን ተከትሎ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ሰሜን ኮሪያ የራሷን ጥቁር ቀለም ያለው ኮካ የመሰለ ምርት የሰራች ሲሆን ‘Cocoa Sparkling’ ስትል ሰይማዋለች። ምርቱ ተመሳሳይ ሽፋን ያለው ይሆን እንጂ ጣዓሙ እንደ ሽፋኑ ተመሳሳይ ነው አይደለም የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡
ግብፅና ፒራሚዶች ከሞላ ጎደል ሚያመሳስላቸው ነገር ያለ ይመስላል፡፡ ፒራሚድ ሲባል ብዙዎቻችን በአእምሯችን የምትመጣው ግብጽ ነች፡፡ ነገርግን ሱዳን ከግብጽ ይልቅ በብዛት ፒራሚዶች የሚገኙባት ሀገር ስለመሆኗ እሙን ነው፡፡

በሱዳን የሚገኘው ኑቢያ 255 ፒራሚዶች አሉት በግብፅ ውስጥ ካለው ቁጥር በእጥፍ ይበልጣል፡፡ የግብፅን 25ኛ ሥርወ መንግሥት ከገዙ በኋላ፣ የኑቢያን ፈርዖኖች ወደ ሱዳን ሸሽተው የኩሽ መንግሥትን መስርተው ነበር፡፡ በሱዳንም የግብፅን ባህል በአዲስ ከተማቸው ውስጥ አስፋፉ።ነገር ግን በሱዳን ውስጥ የሚገኙት የኑቢያን ፒራሚዶች ግብፅ ውስጥ እንዳሉት በስፋት አይጎበኙም።
በሰማይ ላይ ቀስተ ደመናን መመልከት የተለመደ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በወንዝ ውስጥ ይህን ማግኘት እንግዳ ነገር ነው፡፡

“የአምስት ቀለማት ወንዝ” በመባል የሚታወቀው የካኖ ክሪስታሌስ ወንዝ በሰማይ ላይ ካለ ማንኛውም ቀስተ ደመና የበለጠ ደማቅ ነው ቀስተ ደመና አለው ይባልለታል።
ይህ አስደናቂ ወንዝ በኮሎምቢያ ሴራኒያ ዴላ ማካሬና ብሔራዊ የተፈጥሮ ፓርክ ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ወንዙ በቢጫ፣ በሰማያዊ፣ በአረንጓዴ እና በቀይ የሚያብብ ሲሆን ከግንቦት እስከ ህዳር ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ ውበቱ ደምቆ ይወጣል፡፡ውሃው ጥልቀት በሌለው በዚህ ጊዜ ውስጥ የበለጠ ደማቅ ቀለሞችን ይመለከታሉ፡፡
የመሬት መንቀጥቀጥ አገራትን የሚያፈራርስ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በአለማችን ላይ ለመሬት መንቀጥቀጥ የማትረታ ከተማ አለች ሲባል እንዴት የሚለው ጥያቄ መነሳቱ ግድ ነው፡፡

ማቹ ፒቹ ጥንታዊት የኢንካ ከተማ በፔሩ የምትገኝ ስትሆን በመሬት መንቀጥቀጥ በተደጋጋሚ ትጠቃለች፡፡ ለዚህም ችግር ብልሃትን ያስተምራል እንዲሉ በወቅቱ የነበሩ ሰዎች አንድ መላ ዘይደዋል፡፡ ኢንካኖች ‘አሽላር ሜሶነሪ’ የሚባል ድንቅ የምህንድስና ቴክኒክን ፈጠሩ፣ ድንጋዮቹ ያለ ኮንክሪት ሙሌት በትክክል እንዲገጣጠሙ ቆራረጧቸው፡፡ ይህም በመሬት መንቀጥቀጥ ወቅት ድንጋዮቹ ወደ መጀመሪያው ቦታቸው ከመመለሳቸው በፊት በቦታው እንዲንቀሳቀሱ አስችሏቸዋል።